የሀገርን ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በገበያ መር፣ በክህሎትና በቴክኖሎጂ የበቃና የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በገበያ መር፣ በክህሎትና በቴክኖሎጂ የበቃና የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 16/2016(ኢዜአ)፦የሀገርን ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በገበያ መር፣ በክህሎትና በቴክኖሎጂ የበቃና የሰለጠነ የሰው ኃይል የማፍራት ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በ22 የስልጠና ዘርፎች ያሰለጠኗቸውን ከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎች አስመርቀዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ በገበያ መር፣ በክህሎትና በቴክኖሎጂ የበቃ የሰው ኃይል ማፍራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ራሱ ተለውጦ ሀገርን የሚለውጥ ዜጋ ማፍራትን ቀዳሚ ተግባር አድርገን እየሰራን ነው ብለዋል።
የቴክኖሎጂ አቅም የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት በመሆኑ በዚህ ረገድ የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የዛሬዎቹ ተመራቂዎች የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ተመራቂዎቹ ለከተማዋ ልማትና እድገት የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሥራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው ተመራቂዎቹ ከደረጃ 2 እስከ 5 ባሉ ደረጃዎች የሰለጠኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለአንድ ሀገር ዕድገት እና ብልጽግና የቴክኒክና ሙያ ክህሎት የታጠቀና ጠንካራ የሥራ ባህልና ሥነ-ምግባር የተላበሰ ትውልድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።
ከለውጡ ወዲህ አዲስ በተቀረጸው የትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በአዲስ እሳቤ እንዲመራ መደረጉን ገልጸዋል።
በተቋማቱ ደረጃቸውን የጠበቁ ወርክሾፖች ፣ መሠረተ ልማቶች፣ የሰው ኃይልና ማሽነሪዎችን በማሟላት የማጠናከር ሥራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል።
በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ የልህቀት ማዕከላትን ማደራጀት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ የኮሌጆቹን የቅበላ አቅም ከ40 ሺህ በላይ ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው ከ100 ሺ ለሚልቁ ዜጎች አጫጭር ሥልጠናዎችን የመስጠት አቅም መገንባት መቻሉን አስረድተዋል።
ከተመራቂዎች መካከል አያንቱ ሮባና አረጋው ብዙዬ በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ሀገራቸውን በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የተሰጠን የተግባር ስልጠና ስራ ለመፍጠር የሚያግዘንን ክህሎት እንድንጨብጥ አስችሎናል ብለዋል፡፡
የዛሬዎቹ ተመራቂዎች 30 በመቶ የንድፈ-ሃሳብ 70 በመቶ የተግባር ሥልጠና የወሰዱና የብቃት ምዘና ፈተና ያለፉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡