የአሊባባ ግሩፕ በኢትዮጵያ የኢኮሜርስ ገበያ ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአሊባባ ግሩፕ በኢትዮጵያ የኢኮሜርስ ገበያ ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ ፤ነሐሴ ፤16 /2016 (ኢዜአ)፦ የአሊባባ ግሩፕ (AliExpress) በኢትዮጵያ የኢኮሜርስ ገበያ ለመጀመር የሚያስችለውን እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ።
የቻይናው አሊባባ ግሩፕ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማህበር ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የኢኮሜርስ ስራ ለመጀመር የሚያስችለውን እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ ያደረገበት መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ(ዶ/ር) የአሊባባ አሊ ኤክስፕረስ በኢትዮጵያ ስራ መጀመሩ ዓለም አቀፋዊ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ሥራ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ እንዲሁም ለዲጂታል ፈጠራና ለኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
አሊባባ ኢትዮጵያውያን ሸማቾችና ነጋዴዎች በአዲሱ የዓለም ገበያ ምርትና አገልግሎትን ለመገበያየትና ኢትዮጵያን ወደ ዓለም አቀፍ ንግድ እንዲገቡ ማስቻሉን አመልክተዋል።
ድርጅቱ የሚያቀርባቸው የዲጂታል መሳሪያዎችና አማራጮችን በመጠቀም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ተዋናይ ለመሆን ያላትን አቅምና ዝግጁነት ማሳየት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢኮሜርስ ሎጂስቲክስ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ቴዎድሮስ አያሌው አየር መንገዱ አሊባባ ግሩፕ በኢትዮጵያ የሚጀምረውን የኢኮሜርስ ስራ ለማሳለጥ የሚያስችል የኢኮሜርስ ሎጂስቲክስ አገልግሎትን የሚሰጥ ማዕከል(ሀብ) ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የአሊ ኤክስፕረስ ቢዝነስ ዳይሬክተር ጄፍሪ ጂያንግ ድርጅቱ በኢኮሜርስ ያለውን ዓለም አቀፍ ልምድ በመጠቀም የኢትዮጵያውያን ሸማቾችንና የንግድ ቦታዎችን እንቅስቃሴ ለማስተሳሰር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማህበር ፕሬዝዳንት ፍቅር አንዳርጋቸው ማህበሩ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እንቅስቃሴ ውጤታማነት ለማገዝ ከሚመለከታቸው እካላት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ገልጸው እንደ አሊባባ ያሉ የኢኮሜርስ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ገበያ መቀላቀላቸው የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው መናገራቸውን ከኢኖቬሽና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።