የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላም እሴት ግንባታ ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው-የጋራ ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላም እሴት ግንባታ ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው-የጋራ ምክር ቤቱ
ዲላ፤ነሐሴ 16/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላም እሴት ግንባታ ያላቸውን ሚና ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ አንደኛ መደበኛ ጉባኤውን በዲላ ከተማ እያካሄደ ነው።
በጉባኤው ብልጽግናን ጨምሮ 18 አገር አቀፍና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ በሰላም እሴት ግንባታና በፌዴራሊዝም ጽንሰ ሃሳብ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተመላክቷል።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ታምራት አሰፋ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላም እሴት ግንባታ የማይተካ ሚና አላቸው።
ጉባኤው በሰላም እሴት ግንባታና በፌዲራሊዝም ፅንሰ ሃሳቦች ላይ የጋራ ግንዛቤና አስተሳሰብ ለመያዝ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ልዩነቶችን በማጥበብ በጋራ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተን በመስራት ሰላምና ልማትን ማጎልበት ይገባናል ያሉት ሰብሳቢው፣ በተለይ በክልሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሰላምና በልማት የተመዘገቡትን ለውጦችን ለማስጠበቅ መስራት ይገባል ብለዋል።
ለዚህም በማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶችን በማጎልበትና በማልማት የክልሉን ሰላም ለማጠናከር በትጋት መንቀሳቀስ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በክልሉ የፖለቲካ ፉክክርና ተሳትፎ የምናደርገው ሰላማችንን ማስጠበቅ ስንችል ብቻ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኅብረት ፓርቲ ተወካይ አቶ ወልዴ ዳና ናቸው።
ክልሉ በጋሞ "ዱቡሻ" በጌዴኦ "ጎንዶሮን" ጨምሮ ለሰላም እሴት ግንባታ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ባህላዊ እሴቶች እንዳሉት ጠቅሰው፣ ይህንንም በአግባቡ መጠቀምና መንከባከብ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ አመራር ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተቀራርበው መስራታቸው የህዝብን ጥያቄ በተደራጀ አቅም ለመመለስ የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ ነው።
የፓርቲዎቹ ተወካዮች ነገ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አረንጓዴ አሻራቸውን እንዲያኖሩም ጥሪ ቀርቧል።