ቀጥታ፡

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ አዋሳኝ ወረዳዎች ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ዝግጅት ተደርጓል

ጎንደር ፤ ነሐሴ 16/2016(ኢዜአ)፡-የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ አዋሳኝ በሆኑ ሁለት ወረዳዎች በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ ሃገር በቀል ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነገ በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ዓሻራችንን እናኑር በማለት መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸው ይታወቃል።

ይህን ተከትሎ የሰሜን ጎንደር ዞን የበኩሉን ለመወጣት በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ አዋሳኝ ወረዳዎች ለሚያከናውነው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

የመምሪያው ምክትል ሃላፊ አቶ ዮሃንስ ይግዛው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የፓርኩ አዋሳኝ በሆኑት ጃናሞራና በየዳ ወረዳዎች የሚተከሉት ችግኞች የፓርኩን ስነ ምህዳርና ብዝሃ ህይወት ለመጠበቅ የሚያግዙ ናቸው፡፡

በአንድ ጀምበር ከሚተከሉት ሀገር በቀል ችግኞች መካከልም የኮሶ ዛፍ፣ ግራርና ውጨና የተባሉ የዛፍ ዝርያዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰው፤ ለዚህም አምስት የተከላ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የጉድጓድ ቁፋሮን ጨምሮ ለተከላ የተዘጋጁ ችግኞችን ወደ ፓርኩ አዋሳኝ ቦታዎች የማጓጓዝ ስራዎች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁንም አስታውቀዋል።

በዕለቱ በሚከናወነው የችግኝ ተከላም ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍ የቅስቀሳ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በዞኑ በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ 459 ሄክታር ቦታ ተለይቶ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ማሩ ቢያድግልኝ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው ክረምት በፓርኩ ክልል ውስጥ በተዘጋጀ 10 ሄክታር መሬት ሀገር በቀል ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።

ብሄራዊ ፓርኩ እንደ አውሮፓ የዘመን ቀመር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት እንዳለው ይታወቃል።

በፓርኩ ውስጥ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፤ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት መገኛ ስፍራ መሆኑ የሚታወቅ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም