ነገ በአካባቢያችን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ተዘጋጅተናል - የድሬዳዋ ነዋሪዎችና የአመራር አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ነገ በአካባቢያችን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ተዘጋጅተናል - የድሬዳዋ ነዋሪዎችና የአመራር አባላት
ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 15/2016 (ኢዜአ)፡- በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል መዘጋጀታቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎችና የአመራር አባላት ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ዓሻራችንን እናኑር በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
"አንድ ከሆንን ከዚህም በላይ እንችላለን፤ በአንድ መንፈስ በመላው ኢትዮጵያ ዓሻራችንን እናኑር" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህም አዋቂዎች ከ20 በላይ፣ ታዳጊዎች ከ10 በላይ ችግኞችን በመትከል ለሀገር ያለንን ፍቅር፣ ለትውልድ ያለንን ስጦታ በተገቢው ስፍራ እንግለጥ ማለታቸው ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎችና የአመራር አባላት አገራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቀኑን በጉጉት እየተጠባበቁ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ታዳጊዋ ኤፍራታ አበበ እንደተናገረችው፤ ከወላጆቿ ጋር ችግኞችን በመትከል ዓሻራዋን ለማሳረፍ ተዘጋጅታለች።
"ወላጆቼ እና መምህራኖቼ የዛፍን ጥቅም አስረድተውኛል፤ሰው የሚኖረው ዛፎች ሲኖሩ መሆኑን ተምሬያለሁ'' የምትለው ታዳጊ ኤፍራታ፤ ''እኔም አራት የብርትኳን ችግኞች ተክዬ ለመንከባከብ ተዘጋጅቻለሁ" ብላለች።
የታዳጊ ኤፍራታን ሃሳብ የተጋሩት እና በዕለቱ በገንደ ሪጌ ገጠር ቀበሌ የተለያዩ ችግኞችን ለመትከል የተዘጋጁት አርሶ አደር መሐመድ ኡስማን ናቸው።
የአረንጓዴ ዓሻራ ዘመቻ ላይ መረባረብ እና ውጤታማ ማድረግ ለድሬዳዋ አርሶ አደሮችም ሆነ ለድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።
ቀደም ሲል በአረንጓዴ ዓሻራ መርኃ ግብር የተከሏቸው ችግኞች አድገው ፍሬውን እየተመገቡ መሆኑንና ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ማገዙን ገልፀው፤ በተለይም በጎርፍ ይጠረግ የነበረው ማሳቸውን መታደግ ማቻላቸውን ነው የተናገሩት።
እነዚህን ጥቅሞች ለማስቀጠል ነገ በሚካሄደው በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የዛፍ እና የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ወይዘሪት ሰላም ለማ በበኩሏ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ከመጠበቅ በዘለለ ድሬዳዋ ተስማሚ አየር እና ምቹ የመኖሪያ ስፍራ እንድትሆን ማገዙን ጠቅሳለች።
በድሬዳዋ ነገ የሚካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር እንዲሳካ ህብረተሰቡን ከማንቃት በተጨማሪ የዘመቻው ተሳታፊ ለመሆን መዘጋጀቷንም ተናግራለች።
''የዛሬ 18 ዓመት በ1998 ዓ.ም በድሬዳዋ ጎርፍ ያስከተለው አደጋ እና ጥፋት አንዱ መንስዔ ተራራማ ስፍራዎች በደን አለመሸፈናቸው ነው'' ያሉት ደግሞ የአስተዳደሩ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማርቆስ ባዩ ናቸው።
ይህንን አደጋ ተከትሎ የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን ማልበስ እና የጎርፍ አደጋን መከላከል ለድሬዳዋ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ሁሉም ነዋሪ ተረድቶ ርብርቡን ማጠናከሩን ገልጸዋል።
በተለይም የአረንጓዴ ዓሻራ ዘመቻ እና የተፋሰስ ልማት ከተጀመሩ ወዲህ የመጡት ለውጦች መሠረታዊ መሆናቸውን ገልፀው፤ ዘንድሮም የተገኘውን ውጤት ለማጠናከር ነገ መላው የአስተዳደሩ ሠራተኞች እና አመራር አባላት ከነዋሪው ጋር በመሆን ችግኝ እንደሚተክሉ ጠቁመዋል።
የአስተዳደሩ ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ አሚን ዑመር በበኩላቸው ነገ በአንድ ጀምበር የፍራፍሬ፣ የውበት፣ የጥላ እና የደን ችግኞችን ለመትከል አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቆ ቀኑን ሁሉም እየተጠባበቀ መሆኑን ተናግረዋል።