ቀጥታ፡

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የሚያስችሉ የቅድመ መከላከል ተግባራት በትኩረት እየተሰሩ ነው- ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2016(ኢዜአ)፦የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የሚያስችሉ የቅድመ መከላከል ተግባራት በትኩረት እየተሰሩ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡፡

የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጉዳዩን በሚመለከት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ስጥተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት፤ ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓትም የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በዓለም የጤና ድርጅት የህብረተሰብ ጤና ስጋት መሆኑ ከተገለፀ ጀምሮ በሽታው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የቅድመ መከላከል ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም መከካል በድንበርና በተመረጡ አካባቢዎች ላይ ቅኝት የማድረግ፣ የልየታ ስራ፤ በሽታውን መመርመር የሚያስችል የላብራቶሪ አቅምን የማሳደግ እንዲሁም የባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ አያይዘውም እስከ አሁን ድረስ በኢትዮጵያ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የተያዘ ሰው አለመኖሩን ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው በሽታው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አክለዋል።

እስከ አሁን ድረስ በ13 አፍሪካ ሀገራት የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ መከሰቱን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም