ቀጥታ፡

የፖሊስ አገልግሎትን በጥናትና ምርምር ለመደገፍ የተከናወኑ ስራዎች የፌደራል ፖሊስን ተልዕኮ የመፈጸም አቅም እንዲጎለብት አድርገዋል

አዲስ አበባ፣ነሐሴ 16፣ 2016 (ኢዜአ)፦የፖሊስ አገልግሎትን በጥናትና ምርምር ለመደገፍ የተከናወኑ ስራዎች የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከልና መቆጣጠር አቅም እንዲጎለብት ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መስፍን አበበ ተናገሩ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መስፍን አበበ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው በፖሊሳዊ ሙያና ክህሎቱ ብቁና ሥነ- ምግባርን የተላበሰ የፖሊስ ኃይል ለማፍራት በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

በዚህም የትምህርትና ስልጠና፣ የጥናትና ምርምር እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን ወደ አንድ ማዕከል ለማሰባሰብ  የሪፎርም ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በፖሊስ ተቋም ውስጥ ያሉ የስልጠና ዘርፎች በአንድ ማዕከል በዩኒቨርሲቲው ስር እንዲደራጁ ተደርጓል ነው ያሉት።

ይህም ዩኒቨርሲቲው በፖሊሳዊ ሙያና ክህሎቱ ብቁ የፖሊስ ኃይል ከማፍራት ባሻገር የአገሪቷን የፖሊስ አገልግሎት በምርምርና በጥናት ለማገዝ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ አሁን በመተግበር ላይ ያሉ የፖሊስ ሪፎርም ስራዎች መነሻ ጥናቶቻቸው በዩኒቨርሲቲ በተደራጀ አግባብ እንዲሰሩ በመደረጉን ነው ያብራሩት።

ቴክኖሎጂ የሚፈጥራቸውን አቅሞችና እድሎች በአግባቡ በመጠቀም የተቋሙን የመፈፀም አቅም ከፍ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በፈደራል ፖሊስ በወንጀል መከላከልና በወንጀል ምርምራ የተመዘገበው ከፍተኛ የመፈፀም አቅም በጥናትና ምርምር በሚደረግ እገዛና ድጋፍ የተገነቡ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በ1939 ዓ.ም አባዲና ፖሊስ ኮሌጅ በሚል ስያሜ ተቋቁሞ የኮሚሽኑ አንጋፋ የትምህርት ተቋም ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ሲሆን፤ ከ1967 እስከ 1999 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ ሆኖ አገልግሏል፡፡

ከ1999 ዓ.ም እስከ 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሚል ስያሜ በኮሌጅ ደረጃ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ የሚያወቅ ሲሆን፤ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሙሉ ዩኒቨርሲቲነት አድጓል፡፡

ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ ጥራት ያለው ጥናትና ስልጠና እንዲሁም የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም