የሀገርን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በገበያ መር፣በክህሎትና በቴክኖሎጂ የበቃና የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በገበያ መር፣በክህሎትና በቴክኖሎጂ የበቃና የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 16፤2016(ኢዜአ)፦የሀገርን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በገበያ መር፣ በክህሎትና በቴክኖሎጂ የበቃና የሰለጠነ የሰው ኃይል የማፍራት ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠኗቸውን ከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎች አስመርቀዋል።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የሀገርን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በገበያ መር፣ በክህሎትና በቴክኖሎጂ የበቃና የሰለጠነ የሰው ኃይል የማፍራት ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
የከተማችንንም ሆነ ሃገራዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ እራሱ ተለውጦ የሚለውጥ ዜጋ ማፍራት ተቀዳሚ ተግባር ተደርጎ እየተሠራ ነው።
የቴክኖሎጂ አቅም የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት በመሆኑ በዚህ ረገድ የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የዛሬዎቹ ተመራቂዎችም የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ለከተማዋ ልማትና እድገት የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
የዛሬዎቹ ተመራቂዎች በ22 የተለያዩ ዘርፎች የሰለጠኑ ሲሆን፤30 በመቶ የንድፈ-ሃሳብ 70 በመቶ ደግሞ የተግባር ሥልጠና የወሰዱ ናቸው።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከንቲባዋን ጨምሮ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊው ጥራቱ በየነ እና ሌሎችም የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።