የሩሲያና የኢትዮጵያን ታሪካዊ ግንኙነት የሚመጥን የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲኖር በትኩረት ይሰራል - ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የሩሲያና የኢትዮጵያን ታሪካዊ ግንኙነት የሚመጥን የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲኖር በትኩረት ይሰራል - ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2016(ኢዜአ)፦የሩሲያ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነጻ ቀጣና ያላቸውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሐ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለጹ።
ዋና ስራ አስፈጻሚው በሩሲያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ሮዛ የሩቅነህ ጋር በበይነ መረብ ውይይት አድርገዋል።
የሩሲያ ባለሃብቶች በግብርና ማቀነባበሪያ፣በማኑፋክቸሪንግ፣ፋርማሲዩቲካል፣ አውቶሞቢልና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ለዚህም ኮርፖሬሽኑ ከኤምባሲው ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
በሩሲያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሮዛ የሩቅነህ ኢትዮጵያና ሩሲያ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ያላቸው ትብብር ታሪካዊ እንደሆነ አንስተዋል።
የሩሲያ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰው ኢንቨስትመንት ለመሳብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ በቀጣይ በሩሲያ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ፎረሞች ለመሳተፍ ፍላጎት ካሳዩ ኢንቨስተሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶች ለማካሄድ እቅድ መያዙ ተጠቁሟል።
በዚህም በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ የሩሲያ ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚሰራ መገለጹን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።