ነገን ዛሬ የመትከል ትጋት፤ ውብ አዲስን የማየት ጉጉት - ኢዜአ አማርኛ
ነገን ዛሬ የመትከል ትጋት፤ ውብ አዲስን የማየት ጉጉት
የ140 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ለመሆን እየተንደረደረች ያለችው አዲስ አበባ እንደ እድሜዋ ማደር ተስኗት የከተሜነት ዝማኔ ጉዞዋ ቀርፋፋ ሆኖ ቆይቷል።
መንግስታት ቢቀያየሩም አዲስን እንደ ስሟ ውብ፣ ጽዱና ዓለም አቀፍ ደረጃዋን የጠበቀች ከተማ ማድረግ አልተቻላቸውም።
ለአብነትም መዲናዋ ስትቆረቆር የነበረው ጥብቅ ደን እየተጨፈጨፈ ሽፋኑ ቁልቁል ተምዘግዝጎ በ2010 ዓ.ም 2 ነጥብ 8 በመቶ ደርሶ ነበር።
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመላ አገሪቱ ያስጀመሩት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተራቆቱ መሬቶች፣ የተጎሳቆሉ ከተሞች ውብ መልክ እንዲኖራቸው እየተደረገ እያደረገ ይገኛል።
የአዲስ አበባም የዚህ ትሩፋት ተቋዳሽ ሆና ህንጻዎች የሚደረደሩባት ብቻ ሳትሆን አረንጓዴ ተክሎችም በየቦታው የሚበቅሉባት ውብ አዲስ እየሆነች ትገኛለች።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባስጀመሩበት ወቅት የአዲስ አበባ የአረንጓዴ ቦታ ሽፋን ዓለም አቀፍ ደረጃውን ያሟላ ከተማ ሊኖረው ከሚገባው አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።
ነገር ግን ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ሥራዎች ሽፋኑን ወደ 17 በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።
በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ዓለም አቀፍ የከተሞች ስታንዳርድ የሚጠይቀውን የ30 በመቶ የአረንጓዴ ሽፋን ዕውን ለማድረግ የተጀመረው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ዮናስ አባተ ባለፉት ስድስት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዓመታት አሻራቸውን እንዳሳረፉ ይገልፃሉ።
በመላ ሀገሪቱ አርብ ነሀሴ 17 ቀን ለሚከናወነው በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዬን ችግኞችን የመትከል መርሀ ግብር መዘጋጀታቸውን ይናገራሉ።
"ያለችን አንድ ሀገር ነች" የሚሉት አቶ ዮናስ፤ ችግኝ መትከል ለም ሀገር መፍጠር፤ ትውልድ ማስቀጠል በመሆኑ በየዓመቱ በጉጉት እንደሚጠብቁና በንቃት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
አረንጓዴ አሻራ ሀገርን ማልማት ራስን ከተለያዩ አደጋዎች መከላከል መሆኑን ገልጸው፤ ሀገርን ለማዳን የማንም ቅስቀሳ አያስፈልገኝም ብለዋል።
ሁሌም ችግኝ የምንተክል ቢሆንም በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከልጆቻቸው ጋር በመሳተፍ የዚህ ታሪክ አካል እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
በዚህ ሀገርን ለም የማድረግ ዘመቻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት መሰረት ቢያንስ 20 ችግኞችን በጥራት ለመትከል ዕለቱን በጉጉት እየጠበቁ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ይመኙሻል ታደሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረ የአንድነት ገመድ ነው፡፡
የኅብረሰቡ ያለማንም ቀስቃሽ በራሱ ፍላጎት የነገዋን ኢትዮጵያ ብሩህ ለማድረግ በነቂስ ወጥቶ ተክሏል፤ የዘንድሮውንም በጉጉት እየጠበቀ ነው ብለዋል።
ዘንድሮ በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል በተያዘው መርሀ ግብር መሰረት በአዲስ አበባም ከንጋት እስከ ምሽት እንተክላለን ብለዋል።
ለዚህም ችግኞችን ከማፍላት ባለፈ ወደ መትከያ ቦታዎች የማጓጓዝና ጉድጓዶችን የማዘጋጀት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በመዲናዋ የመንገድ አካፋዮች፣ አደባባዮች፣ እንዲሁም በተቋማት አካባቢ ለውበት፣ ለምግብነትና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያግዙ ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ መዲናችንን አረንጓዴ የለበሰች፣ ለመኖር የተመቸች የምናደርጋት እኛው ነን ብለዋል።
በዘንድሮው ዓመት በአዲስ አበባ ብቻ 20 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ለመጭው ትውልድ መትከል ብቻ ሳይሆን ትብብር የሚያመጣውን ውጤት እናሳያለን ነው ያሉት።
ለዚህ ደግሞ የሀይማኖት ተቋማት፣ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ አባላት፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችና መላው የመዲናዋ ነዋሪ ከተማ አስተዳደሩ በሚያዘጋጃቸው ቦታዎች አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።