የአሸንዳ በዓል ተጨማሪ የገቢ ምንጭእንደፈጠረላቸው በመቀሌ የባህላዊ አልባሳት ነጋዴዎች ገለፁ

መቀሌ ፤ ነሐሴ 15/ 2016 (ኢዜአ)፡-  የአሸንዳ በዓል ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደፈጠረላቸው በመቀሌ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ  የባህላዊ አልባሳት  ነጋዴዎች ገለጹ። 

የባህል አልባሳት ነጋዴዎቹ እንዳሉት፤ በከተማዋ የአሸንዳ በዓል በሚከበርበት ወቅት ህብረተሰቡ የባህል አልባሳትን ገዝቶ የመጠቀም ልምዱ እየጨመረ መጥቷል።

ይህም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዳጎለበተው ተናግረዋል። 

በመቀሌ በባህላዊ አልባሳት ንግድ  ከተሰማሩ ነጋዴዎቹ መካከል ወጣት ሀይለ ወልዱ በሰጠው አስተያየት፤ በዓሉ ልጃገረዶች በተለያዩ ጌጣ ጌጦች ደምቀውና በባህላዊ አልባሳት ተውበው የሚያከብሩት መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህም  በብዙዎች ዘንድም በጉጉት እንደሚጠበቅ አመልክቷል። 

በዓሉን ለማክበር ጥቂት ቀናት ሲቀሩ ከሌሎች ቀናትና ሳምንታት በተለየ ሁኔታ ባህላዊ አልባሳትን በማቅረብ ገቢን የማሳደግ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጿል። 

‘’ከዚህ ቀደም የአሸንዳ በዓል በሚከበርበት ወቅት ከ20 ሺህ እስከ 30 ሺህ ብር ገቢ አገኛለሁ፤ አሁንም ከዚህ የተሻለ እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ’’ ብሏል። 


 

በተለይ በዚህ በዓል ወቅት ለአገር ውስጥ ምርቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እንደሚያሳድግ የተናገረው ደግሞ በመቀሌ አዲ ሃቂ ክፍለ ከተማ በባህላዊ አልባሳት ንግድ የተሰማራው ወጣት ገብረ ሚካኤል ገብረ ጨርቆስ ነው።

በአሸንዳ የበዓል አከባበር ወቅት በምናገኘው ገቢም ለሌሎችም  የስራ ዕድልን እንፈጥራለን ብሏል። 

ሌላው በከተማዋ በባህል አልባሳት ንግድ ላይ የተሰማሩት  ሃጂ አህመድ ሲራጅ በበኩላቸው ፤ የልጃገረዶች የነፃነት በዓል ከሆነው  የአሸንዳ በዓል ወቅት በፊት ከ50 ሺህ እስከ መቶ ሺህ ብር እንደሚያገኙ ተናግረዋል።


 

አሁንም የተለያየ ዓይነት የአገር ባህል ልብስ በማዘጋጀት ለገበያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። 

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም