በተያዘው በጀት ዓመት ለውጭ አገራት ከሚቀርበው የኃይል ሽያጭ 300 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል - ኢዜአ አማርኛ
በተያዘው በጀት ዓመት ለውጭ አገራት ከሚቀርበው የኃይል ሽያጭ 300 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2016(ኢዜአ)፦በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት ለውጭ አገራት የሚቀርበውን ኃይል ሽያጭ ተደራሽነት በማስፋት 300 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 20 ሺህ 522 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ከውኃ፣ ከንፋስና ከደረቅ ቆሻሻ በማመንጨት ለአገር ውስጥ ለውጭ ገበያ ቀርቧል ብለዋል።
አጠቃላይ ከቀረበው ኃይል 17 በመቶ የሚሆነው የተገኘው ከታላቁ የሕዳሴ ግደብ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ ከቀረበ ኃይል በድምሩ 20 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ ለውጭ ገበያ ከቀረበ የኃይል ሽያጭ 140 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን ተናግረዋል።
ገቢው ከባለፈው በጀት ዓመት አፈጻጻም ጋር ሲነጻጸር የ16 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ጠቁመዋል።
በአገሪቱ አምስት ትልልቅ የኃይል ማመነጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ለአገር ውስጥና ለውጭ ፍጆታ የሚውል ኃይል በማግኘት ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት በዕጅጉ እንደሚያሳድገው ጠቁመዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ለውጭ አገር የሚቀርበውን ኃይል ሽያጭ ተደራሽነት በማስፋት 300 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት መታቀዱን ገልፀዋል።