ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና የኬንያ የመረጃ ተቋማት በድንበር አካባቢና በኬንያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድን አመራሮችና ታጣቂዎች ላይ የጀመሩትን ኦፕሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል የሚያስችላቸውን አቅጣጫ አስቀመጡ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ እና የኬኒያ የመረጃ ተቋማት በድንበር አካባቢ እና በኬኒያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድን አመራሮችንና ታጣቂዎች ላይ የጀመሩትን ኦፕሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል የሚያስችላቸውን አቅጣጫ አስቀመጡ።

የኬኒያ የመረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ኑረዲን መሐመድ ሀጂ የተመራ የልዑካን ቡድን ለስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብቷል፡፡

ዳይሬክተር ጄነራሉ ከሉዕካን ቡድናቸው ጋር ዛሬ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደረሱ የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ የሁለቱ ሀገራት አቻ የመረጃ ተቋማት ከዚህ በፊት በመረጃ ልውውጥ እና በሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት የጋር መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ወደ ስራ መግባታቸውን እና በትብብራቸው መሰረትም የተቋማቱ የስራ ሀላፊዎቸና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እየተገናኙ ሲገመግሙ ቆይተዋል፡፡

በዚሁ መሰረትም የኬኒያ የመረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ኑረዲን መሐመድ ሀጂ ከተቋማቸው ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በበርካታ የጋራ አጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ውይይት እና ግምገማ በማድረግ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ማስቀመጣቸውን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በላከው መረጃ ጠቁሟል፡፡

ሁለቱ ሀገራት ድንበር እንደሚጋሩት ሁሉ የሚጋሯቸው የደኅንነት ስጋቶች እና አብሮ የመልማት አጀንዳዎች እንዳሏቸው በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል።

በአሁኑ ወቅትም በሁለቱ ሀገራት ድንበርና በኬኒያ ውስጥ ገባ ወጣ እያለ የተለያዩ እኩይ ተግባራትን የሚፈጽመውን የሸኔ የሽብር ቡድን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚቻልበት መንገድ ላይ መክረዋል።

ቡድኑ በተለይም ሲፈጽማቸው የነበሩ ዜጎችን የማገት፤ ንብረት የመዝረፍ የማውደምና እንዲሁም የሰዎችን እንቅስቃሴ የማስተጓጎል ስራዎች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የኬኒያ ዜጎችንም ጭምር ችግር ላይ የጣለ መሆኑ እና ይህን እኩይ ዓላማውን ለማክሽፍ እና ለመግታት የጀመሩትን የመረጃ ልውውጥ እና የተቀናጀ ኦፐሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል መወሰናቸውን የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

በተጨማሪም ቡድኑ የተሰማራባቸውን የኮንትሮባንድ ንግድ፤ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፤ ህገወጥ የማዕድን ማውጣትና ማዘዋወር ስራዎችን ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው በዉይይት ወቅት መገለፁን መረጃው ጠቁሟል፡፡

በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢዎች እና በኬኒያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የሸኔ የሽብር ቡድን በቅርቡ ሁለት የኮሪያ ዜጎችን በማገት ለአልሸባብ አሳልፎ መስጠቱ፤ ቡድኑ በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው የአልሸባብ የሽብር ቡድን ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው መሆኑን ያመለከተው መረጃው፤ ሁለቱ የሽብር ቡድኖች በአካባቢው እና በቀጣናው የደቀኑትን የሽብር ስጋት በጋራ ለመከላከልና ለመቀልበስ መወሰናቸውን የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ መረጃ አመልክቷል፡፡

በአካባቢው እና በቀጠናውም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እያካሄዱ ያሉትን የመረጃ ልውውጥና የተቀናጀ ኦፕሬሽን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

በተያያዘ ሁለቱ አቻ የመረጃ ተቋማት በሱዳን ያለው ጦርነት እና አለመረጋጋት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታና ሱዳን ወደ ቀድሞ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ እንድትመለስ በጋራ እንደሚሰሩም መግለፃቸውን የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ መረጃ ያስረዳል፡፡ የሁለቱም ሀገራት ድንበር ተጋሪ በሆነችው ደቡብ ሱዳንም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና እና የተረጋጋች እንድትሆን በጋራ የማገዝ ስራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የወቅቱ ስጋት በሆነው የሳይበር ደኅንነት ላይም በጋራ የጀምሩትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጋራ ግንዛቤ ይዘዋል።

በቀጣይም ሊደርስ የሚችል የሳይበር ጥቃትን በጋራ የመከላከልና የማስቆም የተቀናጀ ስራም ለመስራት ተስማምተዋል።

የሀገራት አሁናዊ ስጋት እየሆነ ያለውን የስነ ልቦና ጦርነትንም ለመከላከል እና መልሶ ለማጥቃት በሚደረግ ጥረት ሁለቱ አቻ የመረጃ ተቋማት በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ተመልክቷል።

በመጨረሻም በኬኒያ የመረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ኑረዲን መሐመድ ሀጂ የተመራው ልዑክ በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎችን እና የአድዋ መታሰቢያ ሙዚየምን የጎበኙ ሲሆን ፤ከጉብኝቱ በኃላም ዳይሬክተር ጄነራሉ በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ ዋና ከተማና የአፍሪካ ህብረት መዲና የሆነችው አዲስ አበባ እንደስሟ ውብ እና ማራኪ እንደሆነች እንደታዘቡ መግለፃቸውን የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም