መንግስት የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬታማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ ነው - ተስፋዬ በልጂጌ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬታማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ ነው - ተስፋዬ በልጂጌ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬታማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) የተመራ ልዑካን ቡድን በቻይና ቤጂንግ እየተካሄደ በሚገኘው የዘላቂ ልማት ግቦች ዓለም አቀፍ ስብሰባ በመሳተፍ ላይ ይገኛል።
ስብስባው በዓለም አቀፉ የፓርላማ ሕብረት (IPU)ና በቻይናው ብሔራዊ የሕዝብ ኮንግረስ (NPC) ትብብር የተዘጋጀ ነው።
በሴሚናሩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የተመራ ልዑካን ቡድን እየተካፈለ ነው።
የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ምህረቱ ሻንቆ (ዶ/ር) እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምስራቅ መኮንን (ዶ/ር) እየተሳተፉ ይገኛል።
በመድረኩ በዘላቂ ልማት ግቦች (SDGs) አፈጻጸም፣ ስኬትና ፈተናዎች ከመላው ዓለም በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት የተውጣጡ የፓርላማ አባላት እየመከሩ ይገኛል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መንግስት የዘላቂ ልማት ግቦችን ከ10 አመት የልማት እቅድ ጋር በማቀናጀት ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በቁርጥኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን የዘላቂ ልማት ግቦችን መሰረት አድርጎ እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ፓርላማዎች የሕግ ማውጣት፣ የበጀት፣ የክትትልና ቁጥጥር ተግባራቸውን በመጠቀም የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ውይይቱ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ፓርላማዎች እርስ በእርስ የሚማማሩበትና ልምድ የሚለዋወጡበት እድል በመፍጠር በግቦቹ አፈጻጸም የተሻለ ውጤት ለማግኘት እንደሚያስችልም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
የተገኙ ስኬቶችን በማስቀጠል ሊጠናቀቅ 6 ዓመት የቀሩትን የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ሀገራት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን በማጠናከር በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በሌላ በኩል በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ተጨማሪ የገንዘብ ሀብትና የገንዘብ እርዳታ በአስቸኳይ እንዲያገኙና በዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ አስተዳደርና የገንዘብ ሥርዓት ፍትሐዊ የሆነ ሚና እንዲኖራቸው በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የበለፀጉ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ አማራጮችን እንዲያሰፉ በመድረኩ እየተካፈሉ ያሉ ፓርላማዎች በትብብር መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ዓለም አቀፍ ስብስባው እስከ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።