ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የፍትሕ ተቋማት ጠንካራ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የፍትሕ ተቋማት ጠንካራና አስተማሪ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ ተገለጸ።

ኢትዮጵያ  በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማለትም የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት ባከናወነችው አበረታች ተግባር በተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ሽልማት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ተሰጥቷታል።

ለዚህ ስኬት አስተዋፅኦ ለነበራቸው አካላት በአዲስ አበባ ሽልማት በተሰጠበት መርኃ ግብር ላይ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)፤ አበረታች ሥራዎች ቢኖሩም አሁንም ሴቶችና ልጆች ላይ አስከፊ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ነው ብለዋል።

ለዚህም በማኅበረሰቡ ዘንድ ያሉ ጎጂ የባህል አስተሳሰቦች፣ የመረጃ ክፍተት፣ የሕግ ማስፈጸም ጉድለትና የግንዛቤ ችግር አባባሽ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጸዋል። 

በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ሰብዓዊ ክብርን የሚጻረሩ፣ ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ አካላዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳትን እንደሚያደርሱ ገልጸው ጥፋተኞች ላይ የሚወሰኑ ቅጣቶች ጠንካራ እንዳልሆኑ ያነሳሉ።

ሚኒስቴሩ ጥቃትን የመከላከልና ጥቃቶች ሲፈጸሙ የሕጎች አፈጻጸም ያሉ ክፍተቶችንና ማሻሻል የሚያስፈልጋቸውን በተመለከተ አገር አቀፍ ጥናት ያደረገ ሲሆን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

በሴቶችና በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች አገራዊ አደጋ እየሆኑ መምጣታቸውን የጠቀሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዳይሬክተር ሳባ ገብረ መድህን ናቸው። 


 

"አስከፊ ጥቃቶችን እየተለማመድንና በቀላሉ ትኩረት ሳንሰጣቸው እያለፍን ነው" ያሉት ዳይሬክተሯ፥ ከአንድ ሰሞን አጀንዳነት እንደማይሻገሩም አንስተዋል።

የግንዛቤ ሥራዎች ተከናውነው ጠንካራ የሕግ አፈጻጸምና ማኅበረሰቡ ጥቃቶችን እንደ ነውር ወስዶ የራሱን ሞራላዊ ቅጣቶች የማይከተል ከሆነ ችግሩ እንደማይስተካከልም ነው የተናገሩት።

 የፍትሕ ተቋማት በሴቶች ላይ ጥቃት በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ ጠንከር ያለና ለተጠቂዎች ትኩረት የሰጠ የፍርድ ሂደትን መከተል እንዳለባቸው ተመላክተቷል።

የፍርድ ቤት ገለልተኛነት የተጠበቀ ቢሆንም በፍርድ አሰጣጣቸው ላይ ያሉ ጉድለቶችን ለማረም በቂ መረጃ የሚያገኙበት አሰራር በቅንጅት እንደሚተገበርና ለዚህም ስትራቴጂ መዘጋጀቱን አንስተዋል።

የሚሰጡ ቅጣቶች አስተማሪና ድርጊቱን ሌሎች እንዳይፈጽሙት የሚያስጠነቅቁ መሆን እንዳለባቸውም አንስተዋል።

ለሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር ሁሉም እንዲቆም ማኅበረሰባዊ ግንዛቤና አስተማሪ ቅጣቶች እንዲወሰኑ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በማህበራዊ ሚዲያ የማይነገሩ ጥቃቶችን መረጃም በየአካባቢው ለማሰባሰብና ለፍርድ አሰጣጥ እንዲመች በነጻ የስልክ መስመርና በዲጂታል የታገዘ የመረጃ ማሰባሰቢያ ስልት እየተተገበረ መሆኑም ተጠቁሟል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም