ቀጥታ፡

የተርኪዬ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ምርምር ፋውንዴሽን ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2016(ኢዜአ)፦የተርኪዬ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ምርምር ፋውንዴሽን ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።

በተርኪዬ የኢትዮጵያ አምባሳደር አደም መሐመድ ከፋውንዴሽኑ የፕሮግራም ዳይሬክተር ጉቨን ሳክ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ የአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ከፋውንዴሽኑ ጋር በትብብር መስራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑም ተገልጿል።

አምባሳደር አደም በውይይቱ ወቅትም ኢትዮጵያ በአፍሪካ የፖለቲካ፣የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ ያላትን ሚና አንስተዋል።

የአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ የአፍሪካን ቀጣይ አመራሮች በእውቀት፣ ክህሎትና በአፍሪካዊ እሴት ቀርጾ ለማውጣት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

አካዳሚው በጋራ የምርምር ፕሮግራም፣በተማሪዎችና በመምህራን ልውውጥ፣በአቅም ግንባታ እንዲሁም የምርምር ውጤቶችንና የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን በተለያዩ መንገዶች ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ከፋውንዴሽኑ ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳለው አመልክተዋል።

የተርኪዬ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ምርምር ፋውንዴሽን የፕሮግራም ዳይሬክተር ጉቨን ሳክ ተቋማቸው በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በከተማ እድገት ፣ በአካባቢያዊ ትስስር፣ ሰላምና ደህንነት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፋውንዴሽኑ ከተለያዩ አገራት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝና ከአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ አንካራ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም