የፌደራል፤ የክልልና የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነሮች በሀገራዊ የፖሊስ የፀጥታ ዕቅድ ላይ ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የፌደራል፤ የክልልና የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነሮች በሀገራዊ የፖሊስ የፀጥታ ዕቅድ ላይ ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2016 (ኢዜአ)፡- የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነሮች በሀገራዊ የፖሊስ የፀጥታ ዕቅድ ላይ ተወያዩ።
በውይይቱ ላይ ሀገራዊ ፀጥታን ለማስፈን በወንጀል መከላከልና በወንጀል ምርመራ መከናወን ያለባቸው አንኳር ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን የፖሊስ ሪፎርም በተሟላ መልኩ እንደሀገር እየተተገበረ መሆኑ ተገምግሞ፤ በቀጣይም የሠራዊቱን አቅም በሁለንተናዊ መልኩ ለመገንባት እና ፖሊስ ከኅብረተሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ከሕዝቡ ጋር የበለጠ ተቀራርቦ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰራ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በውይይቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በ2016 በጀት ዓመት ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈን በሀገራችን የተሻለ ሰላም እንዲረጋገጥ ፖሊስ እንደ አንድ የፀጥታ ተቋም ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑንና በቀጣይም ይህንኑን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
አያይዘውም በ2017 ዓ.ም የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ተቋማት በሀገራችን የሚካሄዱ ሕዝባዊና መንግስታዊ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ ከወዲሁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ተቀናጅተን መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
በቡድን ተደራጅተው የሕዝቡን ሰላም የሚያውኩ የሽብር እና ፅንፈኛ ቡድኖችን ለመቆጣጠር በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ማሳሰባቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።