የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለበርሐዋ ገነት ድሬዳዋ ትርጉሙ ልዩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለበርሐዋ ገነት ድሬዳዋ ትርጉሙ ልዩ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2016(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለበርሐዋ ገነት ድሬዳዋ ልዩ ትርጉም እንዳለው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በድሬደዋ አስተዳደር የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዝግጅት መጠናቀቁም ተገልጿል፡፡
የምሥራቅ ኢትዮጵያዋ ፈርጥ የሆነችዋ ድሬዳዋ ካሏት መገለጫዎች መካከል 'የበርሐዋ ገነት' የሚለው መጠሪያዋ በስፋት ይታወቃል።
ድሬዳዋ በነዋሪዎቿ ድንቅ እሴትና ባሕሏ፣ በብዝሃ መልኳ፣ በመሳጭ ታሪኳ፣ በንግድና ምጣኔ ሀብት ስበት ማዕከልነቷ ለተወላጇቿ ብቻ ሳይሆን በእንግዶቿም ዘንድ በጉጉት የምትናፈቅ ከተማ እንደሆነች በርካቶች ይመሰክሩላታል።
ከማህበረሰባዊ ገፅታዋ ባሻገር በመልክዓ ምድሯ፣ በጎዳናዎቿ የተተከሉ ዛፎቿ መልኳን በሐመልማላዊ ገፅታ የተካች 'የበርሐዋ ገነት' አድርጓታል።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ እና በከተማ አስተዳደሩ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የቴክኒካል ቡድን ሰብሳቢ ኑረዲን አብደላ "በድሬ መኖሪያ ግቢ አንድ ዛፍ አይጠፋም" ሲሉ የነዋሪዎቿን ዛፍ የመትከል ነባር ባህልና ልምድ ያወሳሉ።
በአረንጓዴ አሻራም "ይህን ነባር ባሕል በማስቀጠል በተለይም ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን በመትከል የድሬዳዋን የበርሐ ገነትነት ይበልጥ እናደምቃለን" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ድሬዳዋና አካባቢዋ ዝናብ አጠር፣ በርሐማና የጎርፍ ተጋላጭ በመሆኑ አረንጓዴ አሻራ ከሌሎች ከተሞች በተለዬ ለከተማዋ ልዩ ትርጉም እንዳለውም ነው ያብራሩት፡፡
ባለፉት ዓመታት በተተገበረው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የጎርፍ ተጋላጭነት እንዲቀንስ የራሱ አበርክቶ እንደነበረውም ጠቅሰዋል።
"የምትተክል ሀገር፣ የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከተማ አስተዳደሩ ሶስት ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል አቅዶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚካሄደው የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ መርሐግብርም ዝግጅት መጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡
ለመርሃ ግብሩ የሚሆኑ ቦታዎች ተለይተው ችግኞችን የማጓጓዝ ተግባራት እየተከናወነ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ ከሚተከሉ ችግኞችሕ 35 በመቶ ለምግብነት የሚውሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚከናወነው ስራ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መላው የከተማዋ ነዋሪዎችም ድሬዳዋን አረንጓዴያማ ለማድረግ በዕለቱ ንቅናቄውን ተቀላቅለው አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል።