በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ከመነጨው 20 ሺህ 522 ሜጋ ዋት ሃይል ውስጥ 17 በመቶው ከታላቁ ህዳሴ ግድብ የተገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ከመነጨው 20 ሺህ 522 ሜጋ ዋት ሃይል ውስጥ 17 በመቶው ከታላቁ ህዳሴ ግድብ የተገኘ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2016(ኢዜአ)፦በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ከመነጨው 20 ሺህ 522 ሜጋ ዋት ሃይል ውስጥ 17 በመቶው ከታላቁ ህዳሴ ግድብ የተገኘ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አሰፈፃሚ አሸብር ባልቻ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 20 ሺህ 522 ሜጋ ዋት ሃይል ከውሃ ፣ ከንፋስና ከደረቅ ቆሻሻ በማመንጨት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡
በዚህም 20 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ ለውጭ ገበያ ከቀረበ የኃይል ሽያጭ 140 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከመነጨው አጠቃላይ ኃይል ውስጥ 17 በመቶ የሚሆነው ከታላቁ ህዳሴ ግድብ የተገኘ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ለአገር ውስጥ ፍጆታና ለውጭ ከተላከ ሃይል የተገኘው ገቢ ከባለፈው በጀት ዓመት አፈጻጻም ጋር ሲነጻጸር የ16 በመቶ ጭማሪ እንዳለውም ነው የተናገሩት፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከፍተኛ ሃይል ማመንጨት የተቻለው ከግልገል ጊቤ ሶስትና ከታላቁ ህዳሴ ግድብ እንደሆነም አስረድተዋል።