በክረምት የሕክምና በጎ ፈቃድ አገልግሎት የጤና ስርዓቱን የሚያሻሽሉ ስራዎች ተከናውነዋል - ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
በክረምት የሕክምና በጎ ፈቃድ አገልግሎት የጤና ስርዓቱን የሚያሻሽሉ ስራዎች ተከናውነዋል - ዶክተር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2016(ኢዜአ)፦ በዘንድሮው ክረምት የሕክምና በጎ ፈቃድ አገልግሎት የጤና ስርዓቱን የሚያሻሽሉ ተግባራት መከናወናቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
የልብ ቀዶ ሕክምናና ስልጠና የሰጡ ከሕንድ እና ከአሜሪካ ለመጡ በጎ ፍቃደኞች የእውቅናና የምስጋና መርሐ-ግብር ተካሄዷል።
በጎ ፈቃደኞቹ በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ሆስፒታል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እና ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች አገልግሎቱን ሰጥተዋል።
የሮተሪ ኢንዲያ በጎ ፈቃደኞች ቡድን ከበጎ ፈቃድ ስራው በተጨማሪ የሕክምና ቁሳቁሶችን የሕክምና አገልግሎት ለተሰጠባቸው ሆስፒታሎች ድጋፍ አድርጓል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በኢትዮጵያ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአጠቃላይ የጤና ስርዓቱን ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የበጎ ፈቃድ ቀዶ ሕክምናና ስልጠና ለመስጠት ከሕንድ ለመጡትን የሮተሪ ኢንዲያ ቡድን እንዲሁም ከአሜሪካ ለመጡትን የኸርት አታክ ኢትዮጵያ በጎ ፍቃደኛ ቡድን አባላት ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሚሳተፉና ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ዶክተር መቅደስ በጤናው ዘርፍ የሚደረገው የበጎ ፈቃድ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ሽሪ አኒል ኩማል ራይ ኢትዮጵያና ሕንድ ለዘመናት የዘለቀ ወዳጅነት እንዳላቸው ጠቅሰው አገራቸው የጤና አገልግሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራች መሆኑን አመልክተዋል።
ሕንድ የኢትዮጵያ መንግስት የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ እንዲሆን እያደረገ ያለውን ጥረት እንደምትደግፍ ተናግረዋል።
የኸርት አታክ ኢትዮጵያ ድርጅት መስራች ዶክተር ተስፋዬ ተሊላ የበጎ ፈቃድ ስራው በአገር ውስጥ የልብ ሕክምና አቅምን ለመገንባት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በእውቅና መርሐ ግብሩ ላይ ለኸርት አታክ ኢትዮጵያና ለሮተሪ ኢንዲያ በጎ ፍቃደኞች ቡድን የምስጋና ምስክር ወረቀት መበርከቱን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።