በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ለአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ለአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ
ነቀምቴ/መቱ/ሮቤ/ ቡሌ ሆራ፤ ነሐሴ 15/2016 (ኢዜአ)፡-በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ለአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዝግጅት መጠናቀቁን የዞኖቹ ግብርና ጽህፈት ቤቶች አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነሐሴ 17 ቀን 2016ዓ.ም በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ዓሻራችንን እናኑር በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አንድ ከሆንን ከዚህም በላይ እንችላለን፤ በአንድ መንፈስ በመላው ኢትዮጵያ ዓሻራችንን እናኑር ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህም አዋቂዎች ከ20 በላይ፣ ታዳጊዎች ከ10 በላይ ችግኞች በመትከል ለሀገር ያለንን ፍቅር፣ ለትውልድ ያለንን ስጦታ በተገቢው ስፍራ እንግለጥ ማለታቸው ይታወቃል።
ይህንኑ ተከትሎ ኢዜአ የምስራቅ ወለጋ፣ የኢሉ አባቦር፣ የባሌና የምዕራብ ጉጂ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊዎችን አነጋግሯል።
የምስራቅ ወለጋ ዞን ግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስፋው ሀምቢሳ እንደተናገሩት ነሐሴ 17 ቀን 2016ዓ.ም ለሚካሄደው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ይከናወናል።
በእለቱም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፤ በዚህም ለደንነት ከሚውሉ በተጨማሩ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች በስፋት የሚተከሉ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁንም የችግኝ ተከላ ቦታን መለየት፣ የጉድጓድ ዝግጅት እንዲሁም መርሃ ግብሩን የሚያስፈጽሙ ኮሚቴዎችን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል።
የዞኑ ዋዩ ቱቃ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ፍቃዱ ገመዳ፣ በወረዳው የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ በማልማት ለኑሮም ሆነ ለእርሻ ስራ ምቹ ሁኔታ የመፍጠሩ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የወረዳው ነዋሪዎችም በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ ሙሉ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።
በተመሳሳይ የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የደን፣ የፍራፍሬ እና ቀርከሃን የመሳሰሉ ችግኞች በስፋት እንደሚከተሉ ገልጿል።
የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ መልካሙ ጫሊ፣ በእለቱ ዘመቻውን ለማከናወን አስፈላጊዎቹ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
''እስካሁን በተሰራው ስራም የመትከያ ቦታዎች ፤ የችግኝ ጉድጓዶችም ተዘጋጅተዋል፤ ችግኞችም ወደ መትከያ ስፍራዎቹ ተጓጉዘዋል'' ብለዋል።
በችግኝ ተከላው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ የኅብረተሰብ ንቅናቄ እና ግንዛቤ ማሳደጊያ ስራዎች በስፋት መከናወናቸውም አንስተዋል።
በዞኑ የመቱ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢዮብ ዝናቡ፣ የወረዳው ህዝብ በቅድመ ዝግጅት ስራው ከመሳተፍ ጀምሮ የሚጠበቅበትን ሲወጣ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
በዞኑ በኖጳ፣ በቾ፣ አሌ፣ ሀሉ እና በሌሎች ወረዳዎችም በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የየወረዳዎቹ የግብርና ጽሕፈት ቤቶች አስታውቀዋል።
የባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤትን በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።
በጽህፈት ቤቱ የተፋሰስ ልማትና የደን እንክብካቤ ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ ኦሊቃ እንዳሉት፤ በዞኑ በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ የሚከናወንባቸው 18 ጣቢያዎች ተለይተዋል።
በዕለቱ የሚተከለው የደንና የፍራፍሬን ጨምሮ ሌሎችም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ወደ መትከያ ስፍራዎች የማጓጓዝ ተግባር መከናወኑን አስረድተዋል።
በዕለቱ በሚደረገው መርሃ ግብር የዞኑን ነዋሪዎች በማስተባበር ችግኝ እንደሚተከል ገልጸው፤ ለዚህም በየደረጃው የተሰማሩ የግብርና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ያደርጋሉ ብለዋል።
በባሌ ዞን የአጋርፋ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል ሐሰን ሱልጣን በሰጡት አስተያየት፣ ችግኝ መትከል ብቻም ሳይሆን ችግኙ እንዲጸድቅ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በዞኑ በህዝብ ተሳትፎ የድርቅ ተጋላጭነትን በዘላቂ ልማት ለመከላከል የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጸው ደግሞ የምዕራብ ጉጂ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ነው።
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ሀላፊ አቶ አያኖ አለማየሁ በመጪው ዓርብ በዞኑ በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የደን፣ የጥላ፣ የፍራፍሬና ለእንስሳት መኖ የሚውሉ ችግኞች በስፋት ይተከላሉ ብለዋል።
ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ካላቸው ችግኞች መካከል የአቮካዶ፣ የፓፓያ፣ የሙዝ፣ የማንጎና ሌሎች የተለያዩ ችግኞች እንደሚተከሉም ጠቅሰዋል።
በዞኑ ዘጠኝ ወረዳዎች 44 የችግኝ መትከያ ቦታዎች መለየታቸውን ገልጸው፤ ለችግኝ መትከያ የተዘጋጁት ቦታዎች ከ8 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት የሚያካልል መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዞኑን የድርቅ ተጋላጭነት በዘላቂ ልማት የህዝብ ተሳትፎ ለመቋቋም የተጀመረው ጥረት አሁንም ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው ብለዋል።
በዞኑ ገላና ወረዳ የቶሬ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጀንበሩ አዳነ፣ የአቮካዶ፣ የሙዝና የማንጎ ችግኝ መትከላቸውን ገልፀው በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለመሳተፍም ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።