ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በሰው ሰራሽ አስተውሎት መስክ በትብብር የመስራት ፍላጎት አላት - አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን - ኢዜአ አማርኛ
ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በሰው ሰራሽ አስተውሎት መስክ በትብብር የመስራት ፍላጎት አላት - አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2016(ኢዜአ)፦ ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ዘርፍ በትብብር መስራት እንደምትፈልግ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ገለጹ።
በአምባሳደር ኢቭጌኒ የተመራ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የባለሙያዎች ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎብኝቷል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታዬ ግርማ (ዶ/ር) ተቋሙ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ያከናወናቸውን ስራዎች አስመልክቶ ለልዑካን ቡድኑ ገለጻ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን የጉብኝቱ አላማ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ያላትን ልምድ መመልከትና የሁለቱን አገራት የቴክኖሎጂ ትብብር ማጠናከር መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርምርና ትግበራ ከፍተኛ ስራ ማከናወኗን ከጉብኝቱ መረዳታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ቴክኖሎጂና ዘመናዊነትን የእድገት መሰረት ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባላቸው ፍላጎት በርካታ ለውጦች በአጭር ጊዜ ውስጥ መምጣታቸውን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የጀመረቻቸውን ስራዎች ሩሲያ ያላትን ልምድ ከማካፈል ጀምሮ በዘርፉ በጋራ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት አምባሳደሩ መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።