በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ

ጂንካ፤ ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (ኢዜአ )፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ውጤት ይፋ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ የ2016 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ውጤትን በማስመልከት ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም በክልሉ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ውጤት ዛሬ ይፋ መሆኑን አብስረዋል።
በክልሉ በ2016 ዓ.ም በመደበኛ፣ በግል፣ በርቀት እና በማታ 122 ሺህ 719 ተማሪዎች ክልላዊ ፈተናውን መውሰዳቸውን አስታውሰዋል
ፈተናውን ከወሰዱ አጠቃላይ ተማሪዎች 42 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት የማለፊያ ነጥብ ማምጣታቸውንም ተናግረዋል።
የማለፊያ መቁረጫ ነጥብ ይፋ መደረጉን የገለጹት ዶክተር አበባየሁ፤ ለመደበኛ ተማሪዎች 50 ፐርሰንት እና ከዚያ በላይ፣ ለልዩ ፍላጎት 45 ፐርሰንት እና ከዚያ በላይ፣ ለአርብቶ አደር አካባቢዎች 48 ፐርሰንት እና ከዚያ በላይ አማካይ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ ክፍል እንደሚሸጋገሩም አስታውቀዋል።
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ በክልሉ በ2016 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ካስፈተኑ 1ሺህ 787 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 164ቱ ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ አሳልፈዋል።
በቀጣዩ የትምህርት ዘመን በተለያዩ ምክንያቶች ደካማ ውጤት ያስመዘገቡ ትምህርት ቤቶችን በመለየት ችግሮቻቸውን ለመፍታት የተጠናከረ ሥራ እንደሚሰራም ዶክተር አበባየሁ ገልጸዋል።
ተማሪዎች https://se.ministry.et/#/result የሚለው ሊንክ ላይ የመለያ ቁጥራቸውን በማስገባት ውጤታቸውን ማየት እንደሚችሉም አስታውቋል።