በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በጋራ ድምጻችንን ልናሰማና ልንሰራ ይገባል- ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በጋራ ድምጻችንን ልናሰማና ልንሰራ ይገባል- ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2016(ኢዜአ)፦ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል፣ ጠንካራ የፍትሕ እርምጃዎች እንዲወሰዱና የግንዛቤ ስራዎች እንዲጠናከሩ በጋራ መስራትና ድምጻችንን ማሰማት አለብን ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት ለሠራችው አበረታች ስራ ባሳለፍነው ሐምሌ ወር በተባበሩት መንግሥታት የሥነ-ሕዝብ ሽልማት ላይ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቷ ይታወቃል።
በዛሬው ዕለትም ኢትዮጵያ ላገኘችው ስኬት አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት የዕውቅና መርሐ ግብር በአደስ አበባ ተካሂዷል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት ህጎች ቢወጡም ከማህበረሰቡ ጋር ጥብቅ የባህል ትስስር ያላቸው በመሆናቸው ድርጊቱን የመከላከል ስራን አዳጋች አድርጎት መቆየቱን አንስተዋል።
በመሆኑም የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማጥፋት ቃል መግባቷንና ቁርጠኛነቷን ማሳየቷን አንስተዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም ያለእድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ብሔራዊ ጥምረት በማቋቋም ሰፋፊ የማህበረሰብ ንቅናቄዎችን እያካሄደ ይገኛል ብለዋል።
የአመስት ዓመት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ውጤታማ ተግባራትን በማከናወን ሀገረን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንድታገኝ ማስቻሉን ገልጸዋል።
የተገኘው ዓለም አቀፍ እውቅና በቅንጅት መስራት ውጤታማ እንደሚያደርግ ያረጋገጥንበት ነው ያሉት ሚኒስትሯ ሆኖም ዛሬም ችግሩ ሙሉ በሙሉ አለመወገዱን ጠቅሰዋል።
ዛሬም ሴት ልጆች ለተለያዩ ጥቃቶችና ለጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሰለባ እየሆኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በመሆኑም በሴቶችና በልጃገረዶች ላይ የሚደርሱ አስገድዶ መድፈር፣ ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለመከላከልና ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ድምጻችንን በጋራ ማሰማት አለብን ብለዋል።
"የልጆቻችንን እንባ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማበስ ዳግም ቃላችንን ማደስና የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ቆርጠን መነሳት ያለብን ለዚህም ጊዜው አሁን ነው" በማለት መልእክት አስተላልፈዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማሕበራዊ ልማት፣ ባህልና ሰፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅ ሰሙ ማሞ፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።