የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በትግራይ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የኃይል መቋረጥ ሊኖር እንደሚችል አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በትግራይ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የኃይል መቋረጥ ሊኖር እንደሚችል አስታወቀ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በትግራይ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የኃይል መቋረጥ ሊኖር እንደሚችል አስታውቋል።
ወደ ተከዜ የኃይል ማመንጫ ግድብ የሚገባውን ውሃ በማስተንፈስ ሂደት የጣቢያው ዩኒቶች ሥራ በማቆማቸው ምክንያት በትግራይ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የኃይል መቋረጥ ሊኖር እንደሚችል ገልጿል።
ከግድቡ ውሃ ሲለቀቅ የሚፈጠረው የእንፋሎት ጭጋግ በትራንስፎርመሮችና የኃይል ማመንጫ ቤቱ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ሁለቱ ዪኒቶች እንዲቆሙ መደረጉን ተቋሙ ገልጿል።
በዚህም የተነሳ የቮልቴጅ መዋዠቅ በማጋጠሙ በትግራይ ክልል አንዳንድ ከተሞች የኃይል መቋረጥ እንደሚያጋጥም ነው ያስታወቀው።
የክረምቱ ዝናብና ወደ ግድቡ የሚገባው የውሃ መጠን እስከሚቀንስ ድረስ ችግሩ ለቀናት የሚቀጥል በመሆኑ የኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች በትዕግስት እንዲጠብቁና ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙም ተቋሙ አሳስቧል።
በዚህም ከግድቡ በላይኛውና በታችኛው ተፋሰስ በሚገኙት በጣንቋ፣ አበርገለ፣ በቆላ ተንቤን፣ በላዕላይ እና ታህታይ ማይጨው፣ በመረብለኸ፣ በአስገደ ጽንበለ፣ በላዕላይና ታህታይ አዲያቦ፣ በመደባይ ዛና፣ በታህታይ ቆራሮ፣ በአጠቃላይ የተከዜ ወንዝ ተዋሳኝ በሆኑ ወረዳዎች ነዋሪዎችና የመስተዳድር አካላት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ መቅረቡን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።