የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሰው ኃይል ልማትና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የላቀ አቅም ገንብቷል- ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ነብዩ ዳኘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሰው ኃይል ልማትና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የላቀ አቅም ገንብቷል- ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ነብዩ ዳኘ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሰው ኃይል ልማትና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የላቀ አቅም መገንባቱን የተቋሙ የሰው ኃብት አስተዳደር ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ነብዩ ዳኘ ገለጹ።
የፌደራል ፖሊሲን የሪፎርም ሥራዎችና አጠቃላይ ዝግጁነት በተመለከተ ኢዜአ በተቋሙ የሰው ኃብት አስተዳደር ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ነብዩ ዳኘ ጋር ቆይታ አድርጓል።
ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራሉ በማብራሪያቸው ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በፀጥታ ተቋማት ላይ በተደረገው የሪፎርም ሥራ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሁለንተናዊ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
ከለውጡ በኋላ በብዙ መልኩ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን ያስታወሱት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራሉ፤ በተለይም በሰው ኃይል የአቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የላቀ ውጤት መምጣቱን አንስተዋል።
እነዚህ ለውጦች ደግሞ በወንጀል ምርመራና በመከላከል ረገድ የሥራ ጥራት፣ ፍጥነትና የቁጥጥር አቅምን በማሳደግ የፖሊስን ሥራ የተሳካ እንዲሆን አድርገዋል ነው ያሉት።
በወንጀል መከላከልና በመረጃ አሰባሰብ የፖሊስን ብቃት ከማሳደግ ባለፈ የሰው አልባ አውሮፕላን(ድሮን)፣ የሞባይል መተግበሪያ፣ የደኅንነት መቆጣጠሪያ ካሜራዎች (ሲሲቲቪ) እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን ገልፀዋል።
በቴክኖሎጂ ትግበራና የሰው ኃይል ልማት በውጭና በአገር ውስጥ የትምህርትና ሥልጠና ሥራዎች በስፋት መከናወናቸውንና ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
የማሻሻያ ስራው የወንጀል ምርመራ ሥራ በአስተማማኝ መረጃና ማስረጃ ተደግፎ የሰዎችን መብት ባከበረ መልኩ እንዲከናወን አስችሏል ብለዋል።
ከለውጡ በፊት በአመራር ቁመና፣ ሎጂስቲክስ፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የሰራዊቱ የመፈጸም አቅም ላይ የነበሩ ክፍተቶችን በጥናት በመለየት ዘርፈ ብዙ የለውጥ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
በፌደራል ፖሊስ በሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ ልማት የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ማሳደሩን በተለያዩ ማሳያዎች መረጋገጡንም ጠቅሰዋል።
በወንጀል መከላከል የኅብረተሰቡ ተሳትፎና እገዛ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ በቀጣይም ይህ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።