ቀጥታ፡

የአየር ንብረትን በትክክል የመተንበይ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል- አቶ ፈጠነ ተሾመ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2016(ኢዜአ)፦ የኢንስቲትዩቱ የአየር ንብረትን በትክክል የመተንበይ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የኢትዮጵያ ሜትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ገለጹ፡፡

አቶ ፈጠነ ተሾመ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በበርካታ ስፍራዎች ከፍተኛ አቅም ያላቸው የአየር ትንበያ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች ተተክለዋል፡፡

ጥራት ያላቸው መረጃዎችን የሚሰበስቡ ዘመናዊ የአየር ንብረት መከታተያ እና መቆጣጠሪያ ራዳሮችም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መገጠማቸውን አንስተዋል፡፡

ከዓለም የሜቲዎሮሎጂ ድርጅት ጋር የሳተላይት መረጃዎችን የመለዋወጥ ባህል እየዳበረ መምጣቱንም እንዲሁ፡፡

ለሰው ኃይል አቅም ግንባታም ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራበት እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የአደጋ ስጋት ያለባቸውን ስፍራዎች በመለየት የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

በአጠቃላይ ኢንስቲትዩቱ የአየር ንብረትን በትክክል የመተንበይ እና የአደጋ ስጋት ያለባቸው ስፍራዎችን በመለየት አስተማማኝ መረጃዎችን የመስጠት አቅሙ እያደገ መምጣቱን ነው የገለጹት፡፡

የአየር ንብረትን በትክክል የመተንበይ አቅም ማደግ ተቋማት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ቀድሞ በመረዳት መፍትሄ ለመስጠት እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡

በተለይም አርሶና አርብቶ አደሩ በየጊዜው ከኢንስቲትዩቱ የሚሰጡ መረጃዎችን ጥቅም ላይ እያዋሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም