ቀጥታ፡

በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍ  አባ ገዳዎችና  ሃደ ሲንቄዎች ጠየቁ

አዳማ ፤ ነሐሴ 15/2016(ኢዜአ)፦ የፊታችን ዓርብ በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የተለመደውን ተሳትፎ እንዲያደርግ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ኅብረት አባላት ጥሪ አደረጉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ነሐሴ 17 ቀን 2016ዓ.ም በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል አሻራችንን እናኑር በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አንድ ከሆንን ከዚህም በላይ እንችላለን፤ በአንድ መንፈስ በመላው ኢትዮጵያ አሻራችንን እናኑር ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህም አዋቂዎች ከ20 በላይ፣ ታዳጊዎች ከ10 በላይ ችግኞች በመትከል ለሀገር ያለንን ፍቅር፣ ለትውልድ ያለንን ስጦታ በተገቢው ስፍራ እንግለጥ ማለታቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴ አሻራ ማኖርን ጥሪ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ የኦሮሞ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች መላው የክልሉ ህዝብ በችግኝ ተከላው የተለመደውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ከኦሮሞ አባ ገዳዎች ኅብረት መካከል አባ ገዳ ረታ ያኢ ለኢዜአ እንደገለጹት  የገዳ ሥርዓት የአረንጓዴ አሻራ ልማትን የሚደግፍና የሚያጠናክር ነው። 

በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ባለፉት ዓመታት በተተከሉ ችግኞች ርጥበት፣ ዝናብና በቂ ውሃ እንዲሁም ጥሩ አየር እንዳስገኘም ገልጸዋል።

እሳቸውም  በአዳማ ከተማ ከደን ችግኞች በተጨማሪ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓያና ሌሎች ለምግብነት የሚያገለግሉ ችግኞች በስፋት መትከላቸውን ተናግረዋል።

ነሐሴ 17 ቀን 2016ዓ.ም  በሚካሄደው አገራዊ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ  ኅብረተሰቡ ችግኞችን እንዲተክል  አባገዳ ረታ ጠይቀዋል። 

ለችግኞቹ እንክብካቤ በማድረግ  እንዲጸድቁ በማስታወስ።

የቱለማ ኦሮሞ ሃደ ሲንቄ አፀዱ ቶላ በበኩላቸው ዛሬ ስንተክል ነጋችንን ነው የምንተክለው ይላሉ።


 

ሃደ ሲንቄዎችና  አባ ገዳዎች ጥላ ስር ሆነው ነው እርቅና ሰላምን የሚሰብኩት ያሉት ሃደ ሲንቄዋ፤ ለዚህም አመቺ ሥነ ምህዳር ለመፍጠር ችግኝ መትከል እና ተክሎም መንከባከብ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በተለይም  የአንድ ቀን ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን ለማሳካት የሴቶች አደረጃጀቶችና ኅብረተሰቡ ለጥላና ለደን የሚያገለግልን ችግኝ እንትከል ሲሉ  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሲኮ መንዶ አባ ገዳ አህመድ ገለቶ ካዎም ችግኞች ከተተከሉ ለኑሮ ተስማሚ  የአየር ሁኔታ፣ በቂ ዝናብና በቂ ውሃ  ለማግኘት ከመቻል ባለፈ፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል።


 

ዋርካ የቆረጠ ሰው በኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ጉማ/ካሣ/ ይወሰንበታል ያሉት አባ ገዳው፣ ጤናማና ጥሩ የአካባቢ ሥነ ምህዳር እንዲኖረን ችግኞችን  መትከልና የተተከሉትን መንከባከብ  ያስፈልጋል።

ለዚህም የፊታችን ዓርብ የሚካሄደውን የአንድ ጀምበር  የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ከንጋት ጀምሮ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍ  አባገዳ አህመድ ጠይቀዋል።

የጅማ ከተማ ነዋሪውና የአገር ሽማግሌ  አቶ ሃጂ ቢያ አባሜጫ  በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በሚያስገኛቸውን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ተጠቃሚ ለመሆን በተከላው ተሳታፊ መሆን ይገባናል ብለዋል።


 

ለዚህም  ሕዝቡ የፊታችን ዓርብ በሚካሄደው አገራዊ ንቅናቄ ከማለዳው ጀምሮ ሁሉም በየአካባቢው በተዘጋጁት የችግኝ መትከያ ቦታዎች ችግኞችን እንዲተክል ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም