በአማራ ክልል የህዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተያዙ ዕቅዶች በላቀ ተነሳሽነት ተፈጻሚ ይሆናሉ-ዶክተር ድረስ ሳህሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የህዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተያዙ ዕቅዶች በላቀ ተነሳሽነት ተፈጻሚ ይሆናሉ-ዶክተር ድረስ ሳህሉ

ባህር ዳር ፤ ነሐሴ 14/2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የህዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በበጀት ዓመቱ የተያዙ ዕቅዶች በላቀ ቁጭትና ተነሳሽነት ተፈጻሚ እንደሚሆኑ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሰሜን ጎጃም ዞን የ2016 ዕቅድ አፈፃፀምና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ ሠላምን ከማስፈኑ በተጓዳኝ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ የተለያዩ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የፀጥታ መዋቅሩ፣ የአመራር አባላትና ህዝቡ ባደረጉት የተቀናጀ ትብብርና ጥረት ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በጠንካራና ብስለት ባለው አመራር ህዝቡን ከችግር ሊያወጡ የሚችሉ ቁርጠኛ የአመራር አባላት ወደ ፊት በማምጣት ሰፊ ርብርብ መደረጉን ተናግረዋል።
በስራዎቹ ሂደት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋትና አዳዲስ አሰራሮችን በማከል በአዲሱ የበጀት ዓመት የላቀ የስራ አፈፃፀም እንዲመዘገብ በየደረጃው የሚገኙ አመራር አባላት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ሰሜን ጎጃም ዞንም በችግር ውስጥ ሆኖ ትምህርት ሊወሰድባቸው የሚችሉ የልማት ተግባራት ማከናወን መቻሉን አብራርተዋል።
አሁንም ሠላምን ለማረጋገጥ ከሚደረገው ብርቱና ያልተቋረጠ ጥረት ባሻገር በ2017 በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፍ የተያዙ ዕቅዶችን በላቀ ቁጭትና ተነሳሽነት እንደሚፈጸሙ ገልጸዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ጥላሁን በበኩላቸው፤ በ2016 የበጀት ዓመት ሠላምን ከማስፈኑ ጎን ለጎን በርካታ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
ለእርሻ ልማት በግብአትነት የሚውል ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት እንደተቻለ ጠቅሰው፤ በገቢ አሰባሰብ፣ በውሃ ተቋማት ግንባታ፣ በመሰረተ ልማትና በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑት ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን አስረድተዋል።
እንዲሁም በጤና መድህን በርካታ አባላትን በማፍራት የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
በአዲሱ በጀት ዓመት ዘላቂ ሠላም በማስፈን ህዝቡ የሚነሳውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በየደረጃው ያሉ የአመራር አባላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ የክልል፣ የሰሜን ጎጃም የዞኑና የወረዳ አመራር አባላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።