ዳያስፖራውን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ ድጋፎች ይደረጋሉ- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራውን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ ድጋፎች ይደረጋሉ- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2016(ኢዜአ)፦ዳያስፖራው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎትና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዳያስፖራውን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ተሳትፎ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈጻሚው ዘመን ጁነዲ ኮርፖሬሽኑ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስተዳደር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ፓርኮቹ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውንና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በፓርኮቹ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችም በፓርኮቹ ውስጥ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግርን በሚያረጋግጡ ዘርፎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ናቸው ብለዋል።
ዳያስፖራው ያካበተውን አቅምና በዘርፉ ያለውን ዕድል ይበልጥ ለመጠቀም ሁለቱ ተቋማት በቅርበት መስራት እንዳለባቸው ነው ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይነህ አቅናው ተቋሙ የዳያስፖራውን ተሳትፎ በማሳደግ ለአገራዊ ልማት ያለውን አበርክቶ ለማጎልበት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሁለቱ ተቋማት ትብብር በኢንዱስትሪ ዘርፍ ዳያስፖራው ያለውን ተሳትፎ ከማሳደግ ባለፈ ኢትዮጵያ መር የሆኑ ውጤታማ የልማት ስራዎችን ለማጠናከር እንደሚያስችል አመልክተዋል።
ተቋሙ ኮርፖሬሽኑ ለዳያስፖራ ተሳትፎ የሚለያቸውን የተሳትፎ ማዕቀፎች (ፓኬጆች) ለማስተዋወቅና በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።