የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አሰጣጥ ሂደት መሻሻል አሳይቷል - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2016(ኢዜአ)፦ የ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያሳየ መምጣቱን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ገለጹ፡፡

የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አፈጻጸም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተገምግሟል።

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ከፀጥታና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በተከናወነው ስራ ባለፉት ሶስት ዓመታት የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል። 

በተለይም የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር የፈተናው ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከተው የፀጥታ ኃይል ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው ተቋሙ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ ፖሊስ ጥበቃ መምሪያን የሪፎርሙ አንዱ አካል አድርጎ በማቋቋሙ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና መጣቱን ገልጸዋል።

የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ ከአጋር የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የተከናወነው የቅንጅት ስራ ከፍተኛ ውጤትና ድል መመዝገቡን መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም