ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ባለሃብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2016(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ባለሃብቶች በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ጥሪ አቀረቡ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና የሥራ እንቅስቃሴ ከሰሞኑ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ለጅቡቲ ወደብ በቅርብ እርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ የገቢ ምርቶች በተፋጠነና ወጪን በቆጠበ መልኩ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል።

በነፃ የንግድ ቀጣናው ሁሉም የመንግሥት አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፤ የምርቶችን ሎጂስቲክስ በማቀላጠፍ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን በማድረግም የላቀ ሚና አለው።

የምስራቁን የኢኮኖሚ ኮሪደር እንቅስቃሴ በማሳለጥና የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ይታወቃል።


 

በመሆኑም የነፃ የንግድ ቀጣናውን የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በድሬዳዋ በመገኘት ጎብኝተዋል።

ለጅቡቲ ወደብ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውና የተለያዩ መሠረተ-ልማቶች የተሟሉለት ነፃ የንግድ ቀጣናው ለአልሚ ባለሃብቶች ዝግጁ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

ለኢንቨስተሮችና ለሠራተኞች የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ መሠረተ-ልማቶችና ህንፃዎች ያሉት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ባለሃብቶች በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ ነፃ የንግድ ቀጣናው በከተማዋ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ የበለጠ እያነቃቃና የሥራ ዕድልም እየፈጠረ ነው ብለዋል።


 

ባለሃብቶች ከጉምሩክ የሚያመጧቸውን ዕቃዎች በደረቅ ወደብ በማራገፍ ለኮንቴነር ኪራይ(ዲመሬጅ) ይከፍሉት የነበረውን ወጪ በማስቀረት የወጪና ገቢ ንግድን እያሳለጠ ስለመሆኑም አንስተዋል።

የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን ተወዳዳሪና ተመራጭ በማድረግ ለአገር ምጣኔ ኃብት እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ ለመጨመር እየተሰራ መሆኑንም ከንቲባው ገልፀዋል።

የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና በ2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተመርቆ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።

የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውኃ አቅርቦት፣ የቴሌኮም አገልግሎት፣ የፍሳሽ ማጣሪያ የተሟላለት ሲሆን፤ ለቢሮና ለንግድ የሚሆኑ የተለያዩ ህንፃዎችን በውስጡ የያዘ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም