ባንኩ ለማላዊ ከ12 ሚሊዮን ዶላር በላይ የድርቅ መደን ዋስትና ክፍያ ፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ ለማላዊ ከ12 ሚሊዮን ዶላር በላይ የድርቅ መደን ዋስትና ክፍያ ፈጸመ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2016(ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ልማት ባንክ ለማላዊ 12 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር የድርቅ መደን ዋስትና ክፍያ ፈጸመ።
ባንኩ ለማላዊ የድርቅ መድን ክፍያውን የፈጸመው ኢሊኖ ባስከተለው ድርቅ ሳቢያ ለደረሰው ጉዳት መሆኑን ኤፒ ዘግቧል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ የመድን ከፍያውን በዚህ ወር ለማላዊ መፈጸሙን ትናንት ማሳወቁንም ዘገባው ጠቁሟል።
ማላዊ በአፍሪካ ልማት ባንክ እና በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ አደጋ አቅም ግሩፕ የድርቅ የመደን ዋስትና እንደነበራት ዘገባው ጠቅሷል።
አገሪቱ ከባንኩ የተከፈላትን የመድን ዋስትና በድርቅ ለተጎዱ 235ሺህ ቤተሰቦች የምግብ እርዳታ እና ከ100 ሺህ ለሚበልጡት ደግሞ ለቀጥተኛ ድጋፍ እንደምታውለው የአፍሪካ ልማት ባንክ ማስታወቁን ዘገባው አመልክቷል።
የማላዊው ፕሬዘዳንት ላዛሩስ ቻክዊራ እንዳሉት፤ ከባንኩ የተገኘው የመድን ዋስትና ክፍያ በኢሊኖ ሳቢያ በተከሰተው ደርቅ ሳቢ የተጎዱ ዜጎችን የሚረዳ ነው ብለዋል።
ከዓለማችን ድሃ ከሚባሉት ሀገሮች አንዷ የሆነችውን ማላዊ ድርቅ የምግብ አቅርቦቷን በተደጋጋሚ ሲያዛባው መቆየቱን ዘገባው አንስቷል።
ማላዊ እ.ኤ.አ ከሰኔ 2023 ጀምሮ በኢሊኖ የተፈጥሮ አደጋ እየተጠቃች እንደምትገኝም ዘገባው አመላክቷል።
በአገሪቱ ከሚገኙ 28 የአስተዳደር ክልሎች ውስጥ 23ቱ የምግብ አቅርቦት መቃወስ ያጋጠማቸው መሆኑንም ጠቅሷል።
በደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የሚስተዋል ዝቅተኛ የዝናብ መጠን በሰብል ልማት ላይ ጉዳት በማድረሱ ከፍተኛ የምግብ አቅርቦት እጥረት እንዳጋጠማት አመልክቷል።