ቀጥታ፡

በክልሉ የ"ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ" ለተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ምክንያት የሆኑ ችግሮችን እየፈታ መሆኑ ተገለጸ

ሆሳዕና፣ ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተጀመረው የ"ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ " ትግበራ ለተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ምክንያት የሆኑ ችግሮችን እየፈታ መሆኑ ተገለጸ። 

ክልል አቀፉ 2ኛ ዙር የ"ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ" መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በመጀመሪያው ዙር ንቅናቄ የተከናወኑ ተግባራት የተለያየ ጥቅም እያስገኙ ነው። 

ንቅናቄው በአመራር ቁርጠኝነትና በህዝቡ ተሳትፎ በመከናወኑ ለተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በመፍታት ውጤት እያስገኘ መሆኑንም ሃላፊዎቹ ተናግረዋል። 

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም እንደገለጹት፣ በዞኑ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ እንዳልነበሩ አስታውሰዋል።


 

በተለይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ የትምህርት ቤቶች ምቹ አለመሆን በመማር ማስተማር ሥራውና በተማሪዎች ውጤት ላይ ተጽኖ ማሳዳሩን ተናግረዋል።  

በክልል ደረጃ የተጀመረው የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ መርሃ ግብርን ተከትሎ በተሰራው ሥራ ከ493 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ ከ421 በላይ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና በአዲስ መልክ የመገንባት ሥራ መከናወኑንም አስረድተዋል። 

ንቅናቄው ከዚህ ቀደም ለተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል በምክንያትነት የሚጠቀሱ ችግሮችን በመፍታት በተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ ጉልህ አስተዋጾ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። 

በንቅናቄው የታየውን ውጤት ለማስቀጠልና የትምህርት ስብራት ለመጠገን በተቀናጀ መንገድ ይሰራል ብለዋል። 

ለእዚህም በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት ከ546 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ በስፋት ለማከናወን ትኩረት መሰጠቱንም አመልክተዋል። 

የስልጤ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሽኩራላህ አህመድ በበኩላቸው፣ ማህበረሰቡን በማሳተፍ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የሚያስችል ንቅናቄ ባለፈው ዓመት መጀመሩን ገልጸዋል። 


 

በእዚህም ከ315 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ለማሰባሰብ እንደተቻለ ተናግረዋል። 

በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ በአዲስ መልክ የተገነቡ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ እና የመማሪያ ግብዓት ተሟልቶላቸው የተሻለ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ እንዳሉ ገልጸዋል።  

ንቅናቄው በትምህርት ቤቶች የሚታዩ ጉድለቶችን በማረም ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ እያገዘ ነው ብለዋል። 

በትምህርት ዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ውጤታማ ሥራዎች መሰራታቸውን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ናቸው። 


 

ንቅናቄው በተጀመረ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ1 ነጥብ 1 በሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል። 

በዚህም እንደ ክልል 1ሺህ 400 በላይ አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች፣ 82 ቤተ መጻህፍት፣ 42 ቤተ ሙከራዎች እና 437 የመጸዳጃ ቤቶችና ሌሎች ግብዓቶች በአዲስ መልክ መገንባታቸውን አስረድተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተገኘውን ውጤት በቀጣይም አጠናክሮ ለማስቀጠል በሁሉም መዋቅሮች ቅንጅታዊ ሥራው መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

ክልል አቀፍ 2ኛ ዙር የ"ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ" መርሃ ግብር የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሴር ብርሃኑ ነጋ እና ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰውን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወራቤ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም