የሶላር ሚኒግሪድ ሃይል ልማትን በማሳደግ የሃይል አቅርቦትና ተደራሽነት ክፍተቱን ለመሙላት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የሶላር ሚኒግሪድ ሃይል ልማትን በማሳደግ የሃይል አቅርቦትና ተደራሽነት ክፍተቱን ለመሙላት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

አዳማ፤ ነሐሴ 14/2016(ኢዜአ)- የሶላር ሚኒ ግሪድ ሃይል ልማትን በማሳደግ የሃይል አቅርቦትና ተደራሽነት ክፍተቱን ለመሙላት እየሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከሁሉም ክልሎች የውሃና ኢነርጂ ቢሮዎች የተወጣጡ ባለሙያዎችን ያሳተፈና በአነስተኛ የሃይል አማራጮች ወይም 'ሚኒ ግሪድ ዲዛይን' የኢነርጂ ልማት ላይ ያተኮረ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ወልዱ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የገጠሩን ማህበረሰብ የዘመናዊ ሃይል አጠቃቀም ለማሻሻል የዘርፉን ባለሙያዎች በክህሎት ማሳደግ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
ሚኒስቴሩ የዘርፉን ባለሙያዎች አቅምና ክህሎት ለማሻሻል ስልጠናዎችን በማጠናከርና የ'ሶላር ሚኒ ግሪድ' የሃይል ልማት በማሳደግ የሃይል አቅርቦትና ተደራሽነት ክፍተቱን ለመሙላት እየሰራ መሆኑንም ስራ አስፈፃሚው አክለዋል፡፡
ይኸውም የ'ሶላር ሚኒ ግሪዶችን' በገጠር አካባቢ የማስተዳደርና የአጠቃቀም ችግሮችን ከወዲሁ ለመፍታት የሚያስችል እውቀት እንዲያካብቱ የተዘጋጀ ስልጠና ነው ሲሉም አጠናክረዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት በተሰራው ስራም 15 የገጠር ከተሞችን የ'ሶላር ሚኒ ግሪድ' የሃይል ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ስልጠና በኋላም ዋናው የኤሌክትሪክ መስመር በማይደርስባቸው የገጠር አካባቢዎች ከ300 -1000 ቤቶች በጋራ ተደራሽ ማድረግ የሚችሉ የ'ሶላር ሚኒ ግሪድ' ማመንጨት የሚችሉበትን ዘዴ ትግበራ ላይ ተመድበው የሚሰሩ መሆኑንም አያይዘው ገልፀዋል፡፡
በውሃና ኢነርጂ ሚስቴር የ'ዩኤንዲፒ "UNDP" ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ይመስላል ተፈራ በበኩላቸው የዋናው የኤሌክትሪክ መስመር የማይደርስባቸውን የገጠር አካባቢዎች የሃይል ተደራሽነት ለማሳደግ የ'ሶላር ሚኒ ግሪድ' ልማት ፕሮጀክት በማስፋፋት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በዚህም በቴክኖሎጂው አጠቃቀምና አተገባበር የታዩ የክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላት ስልጠናው ማስፈለጉንም አክለዋል፡፡
በቀጣይ የ'ሚኒ ግሪድ' ቴክኖሎጂውን ልማት በማስፋፋት ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግና ፍትሃዊ የሃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ ከግል ሴክተሩም ጋር በትብብር ለመስራት የታቀደ መሆኑን አቶ ይመስላል ጠቁመዋል፡፡
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የጋምቤላና የአፋር ክልል የኢነርጂ ባሙያዎች ስልጠናው የሃይል ተደራሽነትን ማጋገጥና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ከማስገንዘብ ጀምሮ በርካታ ስራዎች ለመስራት አነሳስቶናል ብለዋል፡፡
በጋምቤላ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የባዮ ኢነርጂ ባለሙያ አቶ ኡመድ ኡመድ ኡዲያል እንዳሉት ስልጠናው የሃይል ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ላይ የነበረብንን ክፍተቶች የሚሞላና ለስራ የሚያነሳሳ ነው፡፡
አክለውም የኤሌክትሪክ አቅርቦት በማይደርስባቸው ወረዳዎች ላይ ትኩረት በማድረግ አመራሩ ማህበረሰቡና ባለሙያው በመቀናጀት ከግንዛቤ ማስጨበጫ አንስቶ በ'ሶላር ሚኒ ግሪድ' ማስፋፊያ ላይ ለመስራት የሚያስችለንን አቅም የሚገነባ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ ጆር ወረዳ ኡኖጌ ከተማ በ'ሶላር ሚኒ ግሪድ' ትግበራ ላይ የታዩ መልካም ጅምሮችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች በማስፋት ፍትሃዊ የሃይል ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡
ከአፋር ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ በስልጠናው የተሳተፉት የኢነርጂ ባለሙያዋ ወይዘሮ ሰሚራ ኡመር በበኩላቸው በአፋር ክልል አሳይታ ሰመራና ሎጊያ ከተሞች የሶላር ኢነርጂ በስፋት ጥቅም ላይ ቢውልም የማስፋፋት ስራ ግን ይቀራል ይላሉ፡፡
ይህ ስልጠና የ'ሶላር ሚኒ ግሪድ' አጠቃቀም ላይ ሰፊ ግንዛቤ የሰጣቸው መሆኑን ጠቁመው፤ በክልላችንም ይበልጥ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችለንን ክህሎት የሚያስጨብጥ ነው ብለዋል፡፡