ቀጥታ፡

የህብረት ስራ ማህበራት ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማነት አጋዥ እንዲሆኑ ለማስቻል እየተሰራ ነው

አዳማ፤ ነሐሴ 14/2016 (ኢዜአ)፡- የህብረት ስራ ማህበራት የአገር ውስጥ ገበያን በማረጋጋትና የውጭ ግብይት ድርሻቸውን በማሳደግ ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማነት ቁልፍ አጋዥ እንዲሆኑ ለማስቻል እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን የስትራቴጅክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ አቶ ዮሐንስ በቀለ ለኢዜአ እንደገለፁት የህብረት ስራ ማህበራትን አሰራር በማጠናከርና በማዘመን የሀገር ውስጥና የውጭ የግብይት ድርሻቸውን ለማሳደግ የሪፎርም ስራ እየተከናወነ ነው።

በተለይ የፋይናንስ አቅርቦት፣ የብድርና የቁጠባ አቅማቸውን ለማሳደግ፣ የቁጥጥርና የኦዲት ስራዎችን ብቃትና ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ 11 የትኩረት መስኮችን ለይተን እየሰራንበት ነው ብለዋል። 

ሀገር አቀፍ የህብረት ስራ ማህበራት ሪፎርም በእስከ አሁኑ ሂደት በሰባት ክልሎች ተግባራዊ መደረጉንም አንስተዋል።

በዚህም 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ለማሰባሰብ ታቅዶ  7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ መቻሉን ጠቁመው ይህም ሪፎርሙ በጥሩ ጅምር ላይ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል ።

በተመሳሳይ የሀገር ውስጥ ገበያን ለማረጋጋትና የውጭ ግብይት አቅማቸውን ለማሳደግ  በበጀት ዓመቱ  በተሰራው ስራ ውጤት መምጣቱን አመልክተዋል ።

በተለይ አሁን ተግባራዊ በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራን የተሳካ ለማድረግ የህብረት ስራ ማህበራት  የሀገር ውስጥ ገበያን በማረጋጋትና የወጭ ምርቶችን በመጨመር ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ እየሰራን ነው ብለዋል።

በዚህም  7ሺህ 900 በላይ የሚሆኑ የህብረት ስራ ማህበራት የተለያዩ የግብርና ምርቶቻቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ በማድረግ ገበያ እንዲረጋጋ ማድረግ ከመቻሉም ባለፈ  የግብይት ድርሻቸውን 14 ነጥብ 4 በመቶ  ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የህብረት ስራ ማህበራትን የውጭ ግብይት አቅማቸውን ወደ ስድስት በመቶ ማሳደግ መቻሉንም አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ 11 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ቁጠባ ለማሰበሳብ ታቅዶ 15 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ መቻሉን የገለጹት ስራ አስፈፃሚው 880 ሺህ ለሚሆኑ አባላት 17 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብድር መሰራጨቱንም ተናግረዋል።

በዚህም የብድር አገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት ውስጥ 43 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በዘርፉ የተጀመረውን ሪፎርምና የቁጠባ አቅም  በማጠናከር ዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደትና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ውስጥ ሚናችንን እንወጣለን ብለዋል።

የግብርና ምርቱ በስፋት ወደ ገበያ እንዲገባ፣ ዩኒዬኖች ተኪ ምርቶች እንዲያመርቱ፣ የቁጠባና የፋይናንስ አቅማቸው እንዲጠናከር በማድረግ ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ  ውጤታማነት የድርሻችንን እንወጣለን  ሲሉም አክለዋል ።

የህብረት ስራ ማህበራት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት  በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ተግባራት አከናውነናል ያሉት ደግሞ በኮሚሽኑ የህብረት ስራ ግብይት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ንጋቱ ቶላ ናቸው።


 

በተለይ ማህበራቱ የግብርና ምርቶችን በስፋት ወደ ገበያ  በማቅረብ ረገድ የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር ያሉት አቶ ንጋቱ፤ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤፍ፣  የዳቦ ዱቄትና ስንዴ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በስፋት በማቅረብ የነበረውን የአቅርቦት ችግር ማቃለል መቻሉን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የታሰበውን ግብ እንዲያሳካ እቅድ ተዘጋጅቶ ከየክልሎችና የከተማ መስተዳድር የህብረት ስራ ኤጄንሲዎች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

"ከውጭ የሚገቡ የፍጆታ እቃዎች ምርት ከማሰራጨት ባለፈ የግብርና ምርቶችን በበቂ ሁኔታ በማሰባሰብና በማከፋፈል ሊኖር የሚችለውን የአቅርቦት እጥረት ለማቃለል እየሰራን ነው " ብለዋል።

ለዚህም የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒዮኖችን በፋይናንስ፣ በአሰራርና በአቅም ለማጠናክር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ 18 የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒዬኖች የቡና፣ ቅመማ ቅመምና የቅባት እህሎች በስፋት በመላክ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ በትኩረት  እየሰራን ነው  ብለዋል።

በዚህም በማክሮ ኢኮኖሚ የተቀመጠውን የወጭ ምርቶችን የመጨመር ሚና ውስጥ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አመልክተዋል።  

በኮሚሽኑ የህብረት ስራ ማስፋፊያ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ድሪባ በቀለ በበኩላቸው፤ "ዩኒዬኖች የፍጆታ ምርቶችን ከሀገር ውስጥም ሆነ  ከውጭ ጭምር  አስገብተው እንዲያከፋፍሉ በማስቻል የንግድ ስርዓቱን በማስተካከል ፍትሃዊ ግብይት እንዲረጋገጥ ግብ አስቀምጠን እየሰራን እንገኛለን" ብለዋል።


 

ዩኒዬኖችና ማህበራትን የፋይናንስ፣ ምርታማነትና አቅርቦት አቅማቸውን በማጠናከር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ውጤታማነት ቁልፍ አጋዥ እንዲሆኑ ማስቻል አለብን  ሲሉ አስታውቀዋል።

    

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም