የግብርና ግብዓትና ቴክኖሎጂ ተጠቅመን ከምናለማው የመኸር እርሻ የተሻለ ምርት እንጠብቃለን - በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ግብዓትና ቴክኖሎጂ ተጠቅመን ከምናለማው የመኸር እርሻ የተሻለ ምርት እንጠብቃለን - በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አርሶ አደሮች
ሐዋሳ፤ነሐሴ14/2016(ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተገቢውን የግብርና ግብዓትና ቴክኖሎጂ ተጠቅመው በመኸር እርሻ እያለሙት ካለው መሬት የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮች ገለጹ።
በክልሉ በመኸር ለማልማት ከታቀደው ከ540ሺህ ሄክታር በላይ መሬት 90 ከመቶ የሚሆነው በዘር መሸፈኑ ታውቋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን አለም ገበያ ከተማ አስተዳደር የቀዳሻ ቀበሌው አርሶ አደር ሃጂ ቢላል ለኢዜአ እንደገለጹት በ3 ነጥብ 5 ሄክታር መሬታቸው ላይ በርበሬ፣ በቆሎና ስንዴ በመኸር እርሻ እያለሙ ነው።
ከሚያለሙት ሰብል ተገቢውን ምርት ለማግኘት ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና ሌሎች ግብአቶችን መጠቀማቸውን ገልጸው፣ የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ እንዳልተለያቸው ተናግረዋል።
እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ በተያዘው የመኸር እርሻ በግብዓት አጠቃቀምና በማሳ እንክብካቤ የተቀናጀ ስራ በመከናወኑ በአሁኑ ወቅት የሰብሉ ቡቃያ በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል።
በየዓመቱ ምርታማነት እየጨመረ ነው ያሉት አርሶ አደሩ፣ በቆሎ በሄክታር እስከ 60 ኩንታል እንደሚያገኙ ገልጸው፣ "የግብዓት አጠቃቀምና ቴክኖሎጂ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለዋል።"
ከምርት ሽያጩ በከተማ ለንግድ የሚሆን ቤት መስራታቸውን ጠቁመው፣ ከዘንድሮ የመኸር እርሻ እስከ 700 ሺህ ብር ገቢ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
በምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ውድገትና ገፈርሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደቦጭ ታደለ በበኩላቸው በሁለት ክላስተር 111 አርሶ አደሮች ሆነው በ150 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በኩታ ገጠም እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።
ለተከታታይ አራት ዓመታት በኩታ ገጠም ማልማታቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ፣ ኩታ ገጠም ልማቱ ግብዓት በአግባቡ ለመጠቀም፣ የደከሙ አርሶ አደሮችን ለመደገፍና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
በዘንድሮ የመኸር አርሻ አስፈላጊውን የግብርና ግብዓት ተጠቅመው ያለሙት ስንዴ በጥሩ ቁመና ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሄክታር እስከ 70 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
በክላስተር ልማቱ የተሳተፉት ሌላኛው አርሶ አደር አላምረው ፈቃዱ በበኩላቸው በመኸር እርሻ በዋናነት ስንዴ እንደሚያለሙ ገልጸው፣ በአካባቢው ባቄላ፣ ጤፍና ሌሎች ሰብሎችም እያመረትኩ ነው ብለዋል።
የኩታ ገጠም ልማቱ በአርሶ አደሩ መካከል ጤናማ ፉክክር እንዲፈጠር በማድረግ የሥራ ባህልን ከመቀየር ባለፈ ምርታማነት እንዲጨምር እያገዛቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሃይሉ ሰይፉ እንዳሉት በዞኑ 51 ሺህ 489 ሄክታር በጥራጥሬ፣ በዕዝርትና ቅባት ሰብሎች በመሸፈን ዕቅዱን ለማሳካት ተችሏል።
በመኸር ከሚለማው መሬት 33 ከመቶ በስንዴ የሚሸፈን ሲሆን፣ ስንዴን ጨምሮ ጤፍና ገብስን በኩታ ገጠም በማልማት ምርታማነትን ለመጨመር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም ከ25 ሺህ ሄክታር በላይ የስንዴና ገብስ ማሳ በኩታ ገጠም መልማቱን ጠቁመው፣ ዘመናዊ የግብርና አሰራር ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ባለፈ፤ በጋራ የመስራት ልምድን በማሳደግና ብክነት በመቀነስ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው በክልሉ ከ540 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኸር እርሻ ለማልማት ታቅዶ ወደተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
እቅዱን ለማሳካት አርሶ አደሩን ከማዘጋጀት ጀምሮ አስፈላጊ ግብዓት እንዲደርሰው መደረጉንና እስካሁንም 90 ከመቶ የሚሆነው ማሳ በዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል።
ከመኸር ልማቱ ከ49 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ በማሳ ላይ ያለው ሰብል በጥሩ ቁመና እንደሚገኝ ገልጸዋል።