ቀጥታ፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የመካንነት ሕክምና አገልግሎትን ለማስፋት እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2016(ኢዜአ)፦ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የሥነ-ተዋልዶ ሕክምና ማዕከል የመካንነት ሕክምና አገልግሎቱን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።   

ጥንዶች ለአንድ ዓመትና ከዚያ በላይ የወሊድ መከላከያ ሳይጠቀሙ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት እየፈጸሙ ፅንስ መፍጠር ካልቻሉ ቢያንስ በአንዳቸው ላይ የመካንነት የጤና እክል መኖሩን እንደሚያሳይ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል። 

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስድስት ሰዎች በአንዱ መካንነት እንደሚያጋጥም ድርጅቱ ገልጿል።  

በኢትዮጵያ መካንነት እንደ ሕብረተሰብ ጤና ችግር ሳይታይና መፍትሔ ሳይፈለግለት የቆየ ችግር ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትኩረት ተሰጥቶት እንደ ሌሎች የጤና ችግሮች እልባት እያገኘ መጥቷል።

ይህንን የመካንነት ችግር ለመቅረፍም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ አምስት  የሥነ-ተዋልዶ ሕክምና ማዕከል (ሴንተር ፎር ፈርቲሊቲ ኤንድ ሪፕሮዳክቲቭ ሜዲሰን) በአዲስ አበባ ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ላለፉት አምስት ዓመታት በአገልግሎቱ ከ50 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች የተለያዩ ሕክምና እያገኙ መሆኑን የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ክፍል የመካንነት ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ሙስጠፋ ነጋሽ ይገልጻሉ።

ከእነዚህም ውስጥ ከ1 ሺህ 500 የሚበልጡ ጥንዶች በአይ ቪ ኤፍ ሕክምና (የአይ ቪ ኤፍ ሕክምና የሴቷን እንቁላል በመውሰድና የወንዱን የዘር ፈሳሽ በመውሰድ በላቦራቶሪ ጽንሱ ከተፈጠረ በኋላ ወደ ማህጸን የመመለስ ሕክምና ነው) በዚህም ልጅ ማግኘት መቻላቸውን ጠቅሰዋል። 

ይህንን የመካንነት ሕክምና ለመውሰድ የሚመጡ ጥንዶች ሴቷ እድሜዋ ከ35 ዓመት በታች የሚሆን ከሆነ ሕክምናው የተሳካ እንዲሆን በእጅጉ እንደሚያግዝ ገልጸው የመራቢያ አካል ሁኔታዎችም ለህክምናው ስኬት ሌላኛው ምክንያት መሆናቸውንም አንስተዋል።  

ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ ወደ ውጭ ሄደው ሕክምናውን የሚያደርጉ ጥንዶችን አገልግሎቱን በአገራቸው እንዲያገኙ ማድረግ ማስቻሉን ነው ያብራሩት።

ዜጎቻችን በአገራቸው ህክምናውን እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪም ለበርካታ ጎረቤት አገራት ጭምር የህክምና አገልግሎቱን መስጠት መቻሉንም ተናግረዋል።   

ማዕከሉ አሁን ላይ ወደ አምስት ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፤ በቀጣይ በክልሎች ቅርንጫፎችን በመጨመር የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል።   

ለዚህም የመድኃኒት አቅርቦቱንና የሕክምና መሳሪያዎች የማማላት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በዘርፉ ማነቆ የሆኑ የሰው ኃይል ችግር ለመቅረፍም ኮሌጁ ዘርፉ የሚፈልገውን ብቁ ባለሙያ እያሰለጠነ መሆኑንም አብራርተዋል።

ጥንዶች የመካንነት ምልክት ሲያጋጥማቸው በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ማዕከል በመሄድ ማማከርና የሕክምና አገልግሎቱን ማግኘት እንዳለባቸው ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም