ቀጥታ፡

ከተረጅነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት የሴፍትኔት ፕሮግራምን በሽግግር ራስን ለመቻል መጠቀም ይገባል- አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ከተረጅነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት የሴፍትኔት ፕሮግራምን በሽግግር ራስን ለመቻል መጠቀም ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።

በገጠር ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በ1997 ዓ.ም የተጀመረው የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ከ8 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል።

የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ሥር የሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በልማትና ዘላቂ ኃብት ፈጠራ የገቢ ምንጭ በማስገኘት ጥሪት አፍርተው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው።

የመጀመሪያው የልማታዊ ሴፍትኔት መርኃ-ግብር ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ በዘላቂነት ከተረጅነት እንዲወጡ ለማስቻል የተነደፈ ፕሮግራም ነው።

ከዚህም ባሻገር በ2009 ዓ.ም በከተሞች በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን በሥራ ዕድል ፈጠራና ጊዜያዊ እርዳታ ህይወታቸውን በዘላቂነት ለመቀየር በመላ ሀገሪቱ በተመረጡ ከተሞች "የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት" ገቢራዊ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)፤ ከተረጅነት አስተሳሰብ መውጣት ሲባል በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን መርዳት ይቆማል ማለት አይደለም።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ ሲፀድቅ ሰብዓዊ ድጋፍን ማቆም ሳይሆን ለሚገባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገቢ ድጋፍ እንዲደርስ ማድረግን ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።

እንደ ሀገር በሰብዓዊ ድጋፍ ሰበብ ቋሚ ተረጂ የመሆን አባዜ 50 ዓመታትን ተሻግሯል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመውጣት ጸጋዎችን ማልማት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከተረጅነት መውጣት ማኅበራዊ ፍትሕን የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች በተገቢው መንገድ መድረስ የመንግሥት ተቀዳሚ ሥራ መሆኑን ገልፀዋል።

የሴፍትኔት መርኃ-ግብር ለአደጋ የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከችግራቸው በዘላቂነት ለመውጣት የሚታገዙበት በመሆኑ የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ ያግዛል ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ከተረጅነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት የሴፍትኔት ፕሮግራምን በሽግግር ራስን ለመቻል መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሴፍትኔት መርኃ-ግብርን ላልተገባ ዓላማ የሚጠቀሙ አካላት በራሳቸው ሰርተው መለወጥ የሚችሉ ግለሰቦች ቋሚ መጦሪያ ሊያደርጉት እንደማይገባም አሳስበዋል።

በሴፍትኔት መርኃ-ግብር የሚታቀፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ወይም በተደረገላቸው ድጋፍ ከገቡበት ችግር ወጥተው ራሳቸውን መቻል እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ ማስፈጸሚያ አዋጆችና መመሪያዎች እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸው ባልተገባ መንገድ በማዕቀፉ ሥር የነበሩ ግለሰቦች መውጣት አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም