ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቋሚ ኤግዚቢሽን ማዕከል የፊታችን እሁድ ይመረቃል 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2016(ኢዜአ)፦ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የተገነባ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቋሚ ኤግዚቢሽን ማዕከል የፊታችን እሁድ የሚመረቅ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፤ ከነሃሴ 19 እስከ 23 ቀን 2016 ዓ.ም "የኢትዮጵያን ይግዙ" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው የንግድ ሳምንት ኤግዚቢሽን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል። 

ኤግዚቢሽኑ በሚኒስቴሩ ቅጥር ግቢ የሚደረግ ሲሆን በማስጀመሪያው እለት በግሉ ዘርፍና መንግስት ተሳትፎ የተገነባ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቋሚ ኤግዚቢሽን የሚመረቅ መሆኑን ገልጸዋል። 

ከዚህ ቀደም ለሀገር ውስጥ ምርቶች እንጂ የውጭ ንግድ የሚተዋወቅበት የኤግዚቢሽን ማዕከል እንዳልነበር ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።

አሁን ላይ በሚኒስቴሩ ቅጥር ጊቢ የተገነባው ማዕከል ግን በተለያዩ የወጭ ንግድ ምርቶች ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ማሳየት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል። 

በንግድ ሳምንት ከወጪ ንግድ ማዕከሉ በይፋ መከፈት በተጨማሪ አቅራቢ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ለሸማቾች ያቀርባሉ ብለዋል። 

በንግድ ሳምንቱ የፓናል ውይይቶች የሚደረጉ ሲሆን ለንግዱ ማህበረሰብ እውቅና የሚሰጥ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ለመጭው በዓል 115 ሚሊየን ሊትር ዘይት በቀጣዮቹ ቀናት ከጅቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ኮሚቴ ተቋቁሞ በህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አንስተው እስካሁን ከ60 ሺህ በላይ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ያደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም