የወባ መከላከል ሥራዎችን ለማጠናከር 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚገመቱ የፀረ ወባ መድሀኒቶች ይሰራጫሉ - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የወባ መከላከል ሥራዎችን ለማጠናከር 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚገመቱ የፀረ ወባ መድሀኒቶች ይሰራጫሉ - ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2016(ኢዜአ)፦ የወባ መከላከል ስራዎችን ለማጠናከር ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚገመት የፀረ ወባ መድኃኒቶች በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚሰራጩ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) የኢትዮጵያ ልዑክ ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር ከተመራ ልዑካን ቡድን ጋር የወባ መከላከያ አጎበር ግዢ በተመለከተ ውይይት አድርገዋል።
በየጊዜው ዋጋው እየጨመረ የመጣውን አጎበር በአገር ውስጥ ለማምረት ጥረት እንደሚረግም ዶክተር መቅደስ ገልጸዋል።
መንግስት እየተገበረ በሚገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ የሕክምና ምርቶች አምራቾችን ወደ አገር ለመሳብ ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው ከድርጅቶቹ ጋር በአጋርነት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በስርጭት ላይ የሚገኘው አጎበርና የወባ መድኃኒት በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉና በተፈለገው ቦታ ተደራሽ መሆኑን ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) የኢትዮጵያ ልዑክ ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የወባ መከላከያ መድኃኒት የበሽታው ስርጭት በተስፋፋባቸው አካባቢዎች እንደሚሰራጭ ገልጸዋል።
ድርጅቱ የወባ መድኃኒት ተደራሽነትን ለማሳደግ እንደሚሰራና በኢትዮጵያ የወባ መከላከል ስራዎችን መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
በአገር ውስጥ የወባ መድኃኒቶችን ለማምረት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ መናገራቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) የኢትዮጵያ ልዑክ ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር የተመራው ልዑካን ቡድን ትናንት ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ጋር መወያየቱ ይታወቃል።