ሞዛምቢክ የናካላ ወደብ የተወሰነ ክፍል የባህር በር ለሌላት ማላዊ በኪራይ ልትሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሞዛምቢክ የናካላ ወደብ የተወሰነ ክፍል የባህር በር ለሌላት ማላዊ በኪራይ ልትሰጥ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2016(ኢዜአ)፦ ሞዛምቢክ የናካላ ወደብን በከፊል የባህር በር ለሌላት ማላዊ በሊዝ አከራይታ እንድትጠቀምበት የሚያደርግ ስምምነት ተፈራረመች።
የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ፊሊፔ ንዩሲና የማላዊው ፕሬዝዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ ባለፈው ሳምንት የመነሻ ስምምነቶችን መፈራረማቸውን በማሪታይም ኢንዱስትሪ ላይ የሚሰራው የማሪታይም ኤግዚኪዩቲቭ ዘገባ ያመለክታል።
ስምምነቱ የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ተገልጿል።
በተለይም በንግድ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ሌሎች የኢኮኖሚ መስኮች ያለውን ትስስር ለማጎልበት እንደሚያግዝ ተመላክቷል።
ስምምነቱ ማላዊ በሞዛምቢክ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘውን የናካላ ወደብን የተወሰነ ክፍል በሊዝ አልምታ ለገቢና ወጪ ንግድ የመጠቀም መብት ይሰጣታል።
የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ፊሊፔ ንዩሲ ስምምነቱ የሞዛምቢክ-ማላዊ የጋራ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በትብብር ለማልማት እንደሚያስች ገልጸዋል።
ስምምነቱ የአገራቱን የትብብር አድማስ ለማስፋትና ለማጎልበት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የማላዊ ፕሬዚዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ ስምምነቱ የባህር በር የሌላት ማላዊ የናካላ ወደብ እንደ አማራጭ እንደምትጠቀምና ይህም ከዚህ ቀደም አገሪቱ እቃ ለማጓጓዝ የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስ እንደሚያስችላት አመልክተዋል።
የናካላ ወደብ በማላዊ፣ ዛምቢያ እና ሞዛምቢክ በጋራ እየተገነባ ያለ የናካላ ልማት ኮሪደር አካል መሆኑ ተጠቁሟል።
የፕሮጀክቱ ዓላማ ቀጣናዊ ትስስርን በማስፋት ወደብ ሌላቸው ማላዊና ዛምቢያ የባህር በር አማራጭ እንዲያገኙ የማድረግ አላማ አለው።
የናካላ ወደብ በአፍሪካ ከሚገኙ ቁልፍ ደረቅ ወደቦች አንዱ መሆኑን የማሪታይም ኤግዚኪዩቲቭ ዘገባ ያመለክታል።
ከእ.አ.አ 2018 አንስቶ ከጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ(ጃይካ) በተገኘ የ300 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ ወደቡ የማሻሻልና የማዘመን ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል።
የማስፋፊያ ስራው የወደቡን ተርሚናል የማስፋትና የካርጎ አቅሙን የሚያሳድጉ አዳዲስ መሳሪያዎችን መትከልን ያካትታል።
በዓለም ላይ 44 አገራት የባህር በር የሌላቸው ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 16ቱ አፍሪካ ውስጥ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
እ.አ.አ በ1982 በጃማይካ በተካሄደ ስብሰባ የፀደቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የባህር ሕግ የባህር በርና ወደቦችን ሰጥቶ በመቀበል መርሕ የአገራትን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ መጠቀም እንደሚቻል ያስቀምጣል።
የባህር በር የሌላቸው አገራት የባህር በር ካላቸው አገራት ጋር በመነጋገር ተጠቃሚነታቸውን ያረጋገጡባቸው ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መጥተዋል።
የሕግ ማዕቀፉ የባህር በር የሌላቸው አገራት ወደብ ካለበት ቦታ የመድረስና የመመለስ መብት እንዳላቸውም ይደነግጋል።