ቀጥታ፡

ወደ ውጭ የሚላኩ የቅባት እህሎችና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ጥራት ለማሻሻል ጥናትን መሰረት በማድረግ እየተሰራ ነው -ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 13 /2016 (ኢዜአ)፦ ወደ ህንድ የሚላኩ የቅባት እህሎችና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ጥራት ለማሻሻል ጥናትን መሰረት በማድረግ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለፁ።

ኢትዮጵያ ወደ ህንድ በምትልካቸው የግብርና ምርቶች ዙሪያ በግብርና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የህንድ ኤምባሲ በጋራ የተዘጋጀ ጥናት ይፉ ሆኗል።


 

በጥናቱም ኢትዮጵያ ወደ ህንድ በምትልካቸው የግብርና ምርቶች የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ ጥጥ፣ የከበረ ድንጋይ፣ ሻይ እና ቡና በሚመለከት ያሉ እድሎችና ተግዳሮቶች ተዳሰዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩመር እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ምርቶችን ወደ ህንድ የሚላኩበትን ዕድል መለየት እና የኢትዮጵያ ላኪዎች የሚያጋጠሟቸውን ፈተናዎችና እንቅፋቶች በጥናቱ ተመላክቷል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)  በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ወደ ውጭ የሚላኩ  የቅባት እህሎችና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ጥራት ለማሻሻል ጥናትን መሰረት በማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

መንግስት ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በብዛት እና በጥራት ለማቅረብ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከህንድ ጋር ያላት የሁለትዮሽ ንግድ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤  ህንድ  የኢትዮጵያ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬዎች፣ ጥጥ እና ቡና ዋነኛ መዳረሻ ናት ብለዋል።

በግብርና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የህንድ ኤምባሲ ትብብር የተካሄደው ጥናት ወደ ህንድ የሚላኩ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬዎች፣ ጥጥ እና ቡና ጥራታቸውን በማሻሻል የወጪ ንግድ አፈፃፀማችንን ለማሳደግ  ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡

በጥናቱም በቁጥጥር ሂደት ላይ ያሉ የመሠረተ ልማት ችግሮች በመቅረፍ የኤክስፖርት ሂደቶችን ማቀላጠፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩመር በበኩላቸው ኢትዮጵያና ህንድ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የንግድ ትብብር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወደ ህንድ በሚላኩ የግብርና ምርቶች ላይ የተካሄደው ጥናት የሁለትዮሽ ንግድን በተለይም በግብርናው ዘርፍ ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኤክስፖርት አቅም ያላቸውን ቁልፍ ምርቶች፣ የገበያ አዝማሚያዎች፣ የቁጥጥር ማዕቀፎች እና የሎጂስቲክስ ገጽታዎች በመዳሰስ  በሁለቱም ሀገራት ላሉ ባለድርሻ አካላት ጠቃሚ ግብዓት ሆኖ እንደሚያገለግልም ተናግረዋል።

በቀጣይም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር የበለጠ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራም ነው ያነሱት፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም