የዲጂታል ፍኖተ-ሕይወት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና አፍሪካዊያን ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ፍኖተ-ሕይወት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና አፍሪካዊያን ወጣቶች

በአየለ ያረጋል
የሰው ልጅ ምቹ ምድራዊ ህይወት መኖር ይሻል። ላማረ፣ ለሠመረና ለጣመ ኑባሬ ሲል ይራቀቅ፤ ይጠበባል። በዚህ ሂደት ግን በተፈጥሮ ላይ ጨክኗል። ምድራችን በዘመን ዑደት ውስጥ መልኳ ተለዋውጧል። እናም በዛሬዋ ዓለም ሁለት ዐበይት ገጾች ይነበባሉ። በአንድ በኩል ሰው በፀረ-ተፈጥሮ ጭካኔው የአየር ንብረት ለውጥን አባብሶ ገጸ-ምድርን አወይቧል። በሌላ በኩል በሳይንስና ፈጠራ ተራቅቆ የዲጂታል ዓለምን አዋልዶ፤ የሕይወቱን መልክ አድምቋል። እናም ትውልዱ በዕድልና በሳንካ የተወጠረች አንጻራዊ ዓለም ይረከባል። 'ዘውድና ጎፈር' እንዲሉ!!
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የወለደው ድርቅ፣ በርሀማነት፣ ሰደድ እሳት፣ የአንበጣ ወረርሽኝ፣ በሽታ፣ ርሀብ... በጥቅሉ ሁለንተናዊ ቀውስ ተባብሷል። ምድር ሥነ ምሕዳሯ ተዛብቷል፤ መልክዓ ምድሯ ተራቁቷል፤ የአየር ፀባይዋ ዋዥቋል። መጪው ትውልድ ላይ የሚወድቀው ገፈት ደግሞ ከባድ ነው።
በሌላ በኩል ዓለም ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ተራቃለች። የመላው ክፍለ-ዓለም ሰዎች በዲጂታል ዓለም ዘመን ተሳስረዋል። ይህም ምድር ለሰው ልጅ ኑረት የተመቸች እንድትሆን አስቻይ ዕድሎችን እየተፈጠረ ነው። የነገዋ ዓለም ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የዲጂታል መልክ ነው። በተለይ ወጣቱ ትውልድ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ቀማሪም፤ የተዕጽኖው ሰለባም ነው። የሰው ልጅ በ'ነጋዊ' የኑባሬ ዕጣ ፈንታው በዲጂታል ስርዓት መጠርነፉ 'አይቀሬ ሐቅ' ሆኗል።
የዓለም መንግስታት በዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ መምከር ከጀመሩ ውለው ቢያድሩም፤ ከዘላቂ የልማት ግቦች አንኳር ጉዳዮች አንዱ ቢሆንም ዳሩ ምክክር እንጂ ተጨባጭ ገቢራዊ እርምጃ አልተወሰደም በሚል የመፃዒ-ዓለም ትውልድ ተቆርቋሪዎች ድምጽ ጎልቶ ይሰማል። ዕውቋ ስዊዲናዊት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽጽኖ ተሟጋች ታዳጊዋ ግሬታ ቴንበርግ 'ሕልሜን ቀማችሁት' እንዳለችው፤ ወጣቶች ነገ ስለሚረከቧት ዓለም እና ስለተተኪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ አብዝተው ይጮሃሉ። የኅያላን መንግስታትን ቸልተኝነት ይኮንናሉ።
ወጣቶች በመላው ዓለም ስለ አየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች፣ መንስኤዎች እና መፍትሄ-እንከኖች በንቃት ድምጻቸውን ያስተጋባሉ። በተለይም 70 በመቶ ሕዝብ ወጣት በሆነባቸው እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ቀዳሚ ሰለባ በሆኑ አፍሪካን መሰል ክፍለ ዓለማት ቀዳሚ አጀንዳ እየሆነ መጥቷል። ለአካባቢ ጥበቃ እና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ፍትሕ የሚሟገቱ አካላትም በዚያው ልክ እየተበራከቱ መጥተዋል።
አስተዋይ ወጣቶች የሰው ልጅ ሕልውና ላይ ስጋት በደቀነው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ዙሪያ ይመራመራሉ፤ መፍትሔ-እንከን ሃሳባቸውን ተደራሽ ለማድረግ፣ ማህበረሰቡን ለማንቃት፣ ተጽዕኗቸውን ለማጎልበት ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን ወደ መጠቀም አተኩረዋል። ወጣቶች በምድራችን ሁለት መልኮች ውስጥ የተሻለ ነገ እንዲፈጠር እየታተሩ ነው።
በየዓመቱ በፈረንጆቹ ነሐሴ- 12 የሚዘከረው የዓለም ወጣቶች ቀን ከሰሞኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ደረጃ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል። የመታሰቢያ ዕለቱ መሪ ሃሳብም የአየር ንብረት ለውጥን ከዲጂታል ፍኖተ-ሕይወት አኳያ የቃኘ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ 'ከነቁጥ/ጠብታ ወደ እምርታ፡- የወጣቶች ዲጂታል ፍኖተ-ሕይወት ለዘላቂ ልማት (From Clicks to Progress: Youth Digital Pathways for Sustainable Development)" የሚል ነው።
በኢትዮጵያም በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚሰሩ ከ30 በላይ ዓለም አቀፍና ሀገር በቀል ሲቪክ ማህበራትን ያቀፈው 'የአየር ንብረት ለውጥ ጥምረት በኢትዮጵያ" (Consortium for Climate Change- Ethiopia- CCC-E) አዘጋጅነት "ወጣቶችን ለዲጂታል ኢኖቬሽን እና አየር ንብረት ፍትሕ ተሟጋችነት ማነቃቃት" (mobilizing the Youth for Digital innovation and Advocacy for Climate Justice) በሚል መሪ ሃሳብ በትናንትናው ዕለት ተከብሯል። መድረኩ ከየፈርጁ የተውጣጡ ወጣቶችን ባሳተፈ አግባብ የአየር ንብረት ለውጥ ተኮር ስራዎችን በዲጂታል አማራጮች እንዴት ውጤታማ በሆነ መልኩ ማከናወን፣ ንቃትና ግንዛቤ መፍጠር እንደሚቻል ያተኮረ ነበር።
ያሬድ አበራ በተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የወጣት አደረጃጀቶች የሚሳተፍ እንዲሁም 'ዩዝ ፕሪንት' የተሰኘ ሲቪክ ማህበር መስራች ነው። በአየር ንብረት ለውጥ መድረኮች የወጣት ተደራዳሪነት ልምድ አለው። በዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ዘመኑ ጀምሮ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ተጽዕኖ መፍጠሪያ ተጠቅሟል። 'የአረንጓዴ ኢትዮጵያ ንቅናቄ'ን ጨምሮ ዲጂታል አማራጭን ለሃሳቡ ማንጸሪያ በመቀጠም ወጣቶች ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ችሏል። ያሬድ አፍሪካ የራሷን ትርክት እንድታስተጋባና የፖሊሲ ግብዓት ሃሳቦችን ለመፍጠር ወጣቶች ትልቅ ሚና እንዳላችው ይገልጻል። አፍሪካ መራሽ መፍትሔ ለማመንጨትና ተጽዕኖ ለመፍጠር የአፍሪካ ወጣቶች የነቃ ተሳትፎ መጎልበት እንዳለበት ያምናል።
በኢትዮጵያ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲን ጨምሮ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች እንዳሉ በመጥቀስ፤ ነገር ግን ከአስገዳጅነት ወደ አስተሳስብ ለውጥ መሸጋገር እንደሚያዋጣ ይገለጻል። ለአብነትም በኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ ገቢራዊ እየተደረገ ያለው የቆሻሻ አወጋገድ ቁጥጥር መልካም መሆኑን በማንሳት ማህበረሰብ አቀፍ የጽዳትና የአካባቢ ተቆርቋሪነት እሳቤ መያዝ ደግሞ ይህንን የበለጠ ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ ዘላቂ መፍትሄ እንደሆነ ይገልጻል። ለዚህ ደግሞ ወጣቶች ዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም ግንዛቤ ፈጠራ ላይ እንዲሰሩ ይመክራል። በተለይ ማህበረሰቡ በቀላሉ በሚረዳበት መልኩ ይዘት መቅረጽና ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ይናገራል።
የፓን አፍሪካ አየር ንብረት ፍትሕ ጥምረት(ፓክጃ) የአየር ንብረት ፍትህ ክፍል ሃላፊ ኬኒያዊ ቤንሰን ሳምቦ የዓለም ወጣቶች ቀን ከአየር ንብረት አኳያ በተቃኘ አግባብ መከበሩን ያደንቃል። 'የነገዋ ዓለም የወጣቶችና የኢኖቬሽን ዘመን ነው' ይላል። አፍሪካ ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ ያላት አበርክቶ እምብዛም ቢሆንም ግንባር ቀደም የተጽዕኖው ገፈት ቀማሽ መሆኗን ያነሳሉ። ስለዚህ የአፍሪካ ወጣቶች ይህን ሐቅ ተንተርሰው ሕብረተሰቡን ማንቃት፣ ማስተማርና መንግስታት የፖሊሲ ለውጥ እንዲያመጡ የተባበረ ጫና ማሳደር እንደሚችሉ ያምናል። ለዚህ ደግሞ ዲጂታል አማራጮች ሁነኛ ዕድሎች እንደሆኑ ያብራራል። ወጣቶች አደረጃጀታቸውን ማጠናከር፣ ልምድና ተሞክሯቸውን በመጋራት ውጤታማ የአየር ንብረት ፍትሕ ንቅናቄ ማካሄድ እንደሚገባቸው ነው የገለፀው። የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ያለወጣቶች ተሳትፎ እንደማይሳካ በመግለጽም፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች የወጣቶች ሚና ሊጎለብት ይገባል ባይ ነው።
ጆዳሂ በዛብህ ሌላው የአካባቢ ተቆርቋሪ ሲሆን ስለአየር ንብረት ለውጥ የሚሟገት እና ስለምድራችን ደህንነት ዘብ በመቆም የሚታወቅ ወጣት ነው። 'ዘ-ኢንፍለሰር' የተሰኘ ሲቪክ ማህበር በመመስረት የአካባቢ ደህንነትን ጨምሮ ስለአየር ንብረት ለውጥ የአዲሱ ሚዲያን(NEW MEDIA) አማራጭ በመጠቀም ያለመታከት ይሰራል። ወጣቶችን ያነቃቃል። ኮፕን(የዓለም አቀፍ አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ) ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመሳተፍ ልምድ አካብቷል። ጆዳሂ እንደሚለው ዘመን የወለደውን ማህበራዊ ሚዲያ ጨምሮ የተለያዩ የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም የአካባቢ ጥበቃ ሃሳብን ወደ መሬት ለማውረድ ከነቁጥ በመጀመር ወደ እመረታ መሸጋገር ይቻላል። የዲጂታል ፍኖተ ሕይወት ለመማር፣ ለማስተማርና ተፅዕኖ ለመፍጠር እንደሚቻል የራሱን ተሞክሮ ያነሳል።
በራሱ ስም ጀምሮ 'ዘ-ኢንፍለሰር'ን በመመስረት ሃሳቡን ከራሱ ወደ ቅርብ ጓደኞቹ፣ ከዚያ ወደ አካባቢው፤ በመቀጠልም በዓለም ዓቀፍ መድረክ ሳይቀር ሃሳብን ለማንሸራሸር ዕድል አግኝቷል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዲጂታል ሙገታ (digital Advocacy) ጉዞው ዓለም አቀፍ ወዳጀችን የማፍራት፣ በቀላሉ ተጽዕኖ መፍጠር እና ማህበረሰብን ማንቃት እንደሚቻል ተሞክሮ ቀስሟል። በሌላ በኩል ንቅናቄን በወጥነት እና ዘላቂነት ማስቀጠል፣ እምነትና ተአማኒነትን ማሳደር፣ በዲጂታል አማራጭ ተደራሽነትን ማረጋገጥ ፈተናዎች እንደሆኑ ይጠቅሳል። ጆዳሂ አፍሪካ ከ60 እስከ 70 በመቶ ሕዝቧ ወጣቶች ናችው። ይህ ወጣት የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ ስለመጻዒ-ዓለም ፈተና እና ዕድሎች 'በንቃት እንዲሳተፍ አለመቆስቆስ ብክነት ነው' ብሎም ያምናል። እናም ከተፈጥሮ ጋር የተስማማ፣ ከአካባቢው ጋር የተዋደደ ማህበረሰብ ለመገንባት ወጣቶች አይተኬ ሚና እንዳላቸው ጠቅሶ፤ ይህን እንዲጠቀሙ ጠይቋል።
የማርኬቲንግ ባለሙያዋ ቤተልሄም አበበ ሌላዋ የአካባቢ ጉዳዮች አንቂ ወጣት ናት። የዓለም አቀፉ ሮትራክት ድርጅት የኢትዮጵያ ሊቀመንበርም ናት። የወጣቶች ስልጠና፣ ትብብር ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጣ ታምናለች። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አቃቂ አካባቢ ሶስት ኪሎሜትር የሚሆን ወንዝ ላይ እርሷና ወጣት ጓደኞቿ በየሳምንቱ በሚያደርጉት የወንዝ ፅዳት ዘመቻ በሂደት ከነዋሪዎች ጋር መቀራረብ በመፍጠር ማህበረሰብ አቀፍ ለውጥ ማምጣት እንደቻሉ ታወሳለች። ይህም በጽናትና በሰዎች ተገቢ ያልሆነ ግብረ መልስ ባለመበገር በትጋት መስራት እንደሚገባ ታምናለች።
መሰረት ሀብታሙ በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ሳይንስ መምህርትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ ናት። በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ወጣቶች በዲጂታል ሚዲያ ስለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መፍጠር እንደቻሉ የነበራትን የውጭ ሀገር ተሞክሮ ታነሳለች። በአካዳሚክ ዓለም በርካታ ጥናቶች ቢኖሩም ከመደርደሪያ ወደ መሬት መውረድ ላይ ጉድለቶች እንዳሉ ትጠቅሳለች። በቀላል እና ቀልብ በሚስቡ የይዘት አቀራረቦች የአስተሳስብ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ገልጻለች። በሌላ በኩል በአካባቢ ጉዳዮች ላይ የሚሰነዘሩ የተዛቡ መረጃዎችን በማጋለጥና የጠራ አመለካከት እንዲኖር ለማስቻል የወጣቶችና የዲጂታል አማራጮች ትስስር ያለውን ወሳኝ ሚና ትገልጻለች።
ወጣቶቹ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማራጮች ከአካባቢ ጥበቃና ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ የመፍትሄ አማራጮችን ማቅረብ በዋነኝነት የወጣቶችን ተሳትፎና በኃላፊነት መስራት ይጠይቃል ባይ ናቸው። በጥቅሉ የወጣቶቹ ሃሳብና ተሞክሮ ማሰሪያው ቁም ነገር በአዲሱ ዓለም ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን የጋራ ስጋት የሆነውን አየር ንብረት ለውጥ መንስኤዎች፣ ተገዳሮቶችና መፍትሄዎች ዙሪያ ሃሳብን ለማስተጋባት እንዴት መጠቀም ይቻላል የሚል ነው። ለምሳሌ የግሪንሃውስ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ታዳሽ ሃይልን የመጠቀም እንዲሁም በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ የሚያደርጉ ኢንዱስትሪዎች ዘንድ አካላዊ ምርትና አገልግሎትን በዲጂታል መንገድ ማከናወን እንደ መፍትሄ ይነሳል። በሌላ በኩል የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖውን ለመቋቋም ድርቅ የሚቋቋሙ ሰብሎችን መጠቀምና የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ስርዓትን ማጠናከር የሚል ሃሳብም እንዲሁ።
በዚህ ረገድ በተለይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በፖሊሲና አሰራሮች ጭምር በማስደገፍ የሰራቻቸው ስራዎች የሚደነቁ ናቸው። ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የተሰጠው ትኩረት ደግሞ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታከናውናቸውን ስራዎች የበለጠ ለማጠናከርና አርአያነታቸውን ለሌሎች ጭምር በሚገባ ለማድረስ አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራል።
በመሆኑም ጤናማና ዘላቂ አካባቢ ለማረጋገጥ፣ ብክለትን ለመከላከል ብሎም አየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የዘመኑ የቴክኖሎጂና ፈጠራ ውጤቶች ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይገባል። በዚህ ረገድ በሳይንስና ፈጠራ ላይ የሚራቀቁ ወጣቶች አንድም በዚህ ቅኝት እንዲራመዱ፣ አንድም ዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከተፈጥሮ ጋር የሚስማማ ማህበረሰባዊ አስተሳስብ ግንባታ ላይ በስፋት ሊሰሩ ይገባል።