ቀጥታ፡

ለወርቅ ማዕድን ማምረቻ ፕሮጀክት ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 13 /2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኩርሙክ የወርቅ ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የኩርሙክ ወርቅ ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጅ ብሮክስ ወርቁ ናቸው፡፡

የኃይል ማመንጫ ግንባታው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ ወረዳ እንደሚከናወን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትክ ኃይል የገበያና ቢዝነስ ልማት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሕይወት እሸቱ ከኩባንያው ጋር የተካሄደው ስምምነት ለ12 ዓመታት የሚቆይና 35 ሜጋ ዋት ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኃይል አቅርቦት ስምምነት ክፍያው በዶላር እንደሚፈፀምና ይህም የተቋሙን የውጭ ምንዛሬ በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡

ስምምነቱ ከኃይል አቅርቦት ባለፈ ለወርቅ ማምረቻ ፕሮጀክቱ ኃይል ለማቅረብ የሚያግዘውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የዲዛይንና የግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ለተቋሙ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝበትን እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ይህም ተቋሙ በኃይል መሰረተ ልማቶች ግንባታ ሥራ ላይ ያለውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።

ተቋሙ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ለሚገኙ የተለያዩ ዘርፎች አስተማማኝ ኃይል በማቅረብ የኢንቨስትመንት ስራዎችን በመደገፍ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የኩርሙክ ወርቅ ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብሮክስ ወርቁ በበኩላቸው ስምምነቱ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለማግኘት እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።

ተቋሙ በስምምነቱ መሰረት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።

የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካውን በ2018 ዓ.ም ወደ ስራ ለማስገባት ዕቅድ እንደተያዘለት የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ በአሁኑ ወቅትም ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ወደ ቦታው የማጓጓዝ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ዘጠኝ ቶን የሚጠጋ ወርቅ የማማረት አቅም ይኖረዋል የተባለውና የ500 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት እንደሆነ የተነገረለት ይህ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ኩርሙክ ወረዳ እንደሚገነባ ጠቁመዋል።

የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካው ተጨማሪ የኃይል ፍላጎት ሲኖረው በአቅርቦቱና በዋጋው ላይ ማሻሻያ እንደሚደረግበት በውሉ ላይ መካተቱን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም