የኮሪደር ልማት ለታለመለት አገልግሎት ብቻ እንዲውል የወጣው ደንብ በአጭር ጊዜ ለውጥ እያመጣ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 13 /2016 (ኢዜአ)፦የከተማውን ውበትና  ፅዳት ለማስጠበቅና የኮሪደር ልማቱ ለታለመለት አገልግሎት  እንዲውል የወጣው ደንብ በአጭር ጊዜ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  ፅዳት ኤጀንሲ  አስታወቀ።

ኤጀንሲው መልካም አስተዳደርን በማስፈን ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ታሳቢ ያደረገ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር አከናውኗል ። 

በውይይቱ የግል ፅዳት ድርጅቶች ፣ የሽርክና ማህበራት ፣ የክፍለ ከተማ ፅዳት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች እና ብሎክ ተወካዮች ታድመዋል። 

በአዲሱ በጀት ዓመት መልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራርን መከላከል የሚያስችል መነሻ ዕቅድ፣  የከተማዋን ፅዳትና ውበት ለማስጠበቅ የወጣው ደንብ ቁጥር 167/2015 ሪፖርት ፣ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና መከላከል ሪፖርት ለተሳታፊዎች ቀርቧል። 

በመድረኩ የተገኙት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ለማ (ዶ/ር) ኤጀንሲው ከተማዋን ውብና ፅዱ ለማድረግ በቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ረገድ ውጤታማ ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የኮሪደር ልማቱ ለታለመለት አገልግሎት ብቻ እንዲውል በማሰብ የወጣውን ደንብ ህብረተሰቡ ተግባራዊ እያደረገው ይገኛል ብለዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ከዚህ ቀደም የነበረው የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ልማድ እየተለወጠ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡ 

ኤጀንሲው በሚዲያና በፊት ለፊት ግንኙነት የተለያየ ግንዛቤ ፈጠራ በመስራት የሚታይ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የኤጀንሲው ግንዛቤ ስርፀትና ህብረተሰብ ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ሂርጳ ገልጸዋል። 

ደንቡ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 82 ድርጅቶችና 72 ግለሰቦች ደንቡን በመጣስ መቀጣታቸውን በሪፖርቱ ላይ አመላክተዋል ። 

የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ፅዳት አምባሳደር አቶ አበበ ባይሽ ፅዳትና ውበት ከቤት ጀምሮ እስከ ከተማ የሚዘልቅ በመሆኑ ለከተማዋ ሁለንተናዊ ጽዳት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል ። 

በከተማዋ ተግባራዊ የተደረገው ደንብ ተገቢና የከተማዋን ውበት በዘላቂነት የሚያስጠብቅ ነው ብለዋል።

የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ነዋሪና የአዲስ ታምሩና ጓደኞቹ ሽርክና ማህበር አባል አቶ መንግስቱ ደሳለኝ መድረኩ ስራችንን በትጋትና በጥንካሬ በማከናወን የከተማችንን ውበትና ጽዳት በሚገባው ልክ እንድናስጠብቅ ግንዛቤ ፈጥሮልናል ብለዋል፡፡

የቅብብሎሽ ጣቢያ እጥረት እና የሽርክና ማህበራት ቆሻሻ ማቆያ ቦታ በየጊዜ መቀያየር ለስራቸው አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ተሳታፊዎቹ በስፋት አንስተዋል።

ኤጀንሲው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን በቅንጅትና በትብብር በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም