የአፍሪካ የከተሞች ፎረም የኢትዮጵያ ከተሞችን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል - ጫልቱ ሳኒ  

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 13/ 2016 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ የከተሞች ፎረም በኢትዮጵያ ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ ልማቶችንና መልካም ገጽታዎችን ለማስተዋወቅ እድል እንደሚፈጥር የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ።  

የአፍሪካ የከተሞች ፎረም "ዘላቂ የክትመት ምጣኔ ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063" በሚል መሪ ሀሳብ ከነሐሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ኢትዮጵያ በከተማ ልማት ዘርፍ እጅግ አበረታች ስራ እያከናወነች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ከአዲስ አበባ በተጨማሪም በ31 ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ከዚህ አኳያ የፎረሙ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ የተሰሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን፣ፓርኮችን እና ሌሎች ፕሮጀክቶችን እንደሚጎበኙ ጠቁመዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያን መልካም ገጽታን ለማስተዋወቅና የልምድ ልውውጥ ለማካሄድ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከተሞች የተከናወኑ ስራዎችም ለሌሎች አፍሪካ ከተሞች መልካም ምሳሌ እንደሚሆኑም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም ላይ የተገኙ የተለያዩ ተሞክሮዎች የሚቀርቡ ሲሆን በተጨማሪም ከተሞች በዲጂታል ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ከተሞች ያላቸውን ጸጋዎች የሚያስተዋውቁበት፣የኢንቨስትመንት አማራጮች መሸጥ የሚችሉበት እድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡ 

የቴክኒክ፣የእውቀት እና የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘትም የእርስ በእርስ ትውውቅ እና ግንኙነት የሚፈጠርበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በፎረሙ በርካታ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት በመሆኑ ከከተሞች ሥኬት እና ፈተናዎች ልምድ እንደሚወሰድበትም ነው ያብራሩት፡፡

ከፎረሙ የሚገኙ የፖሊሲ ምክረ ሀሳቦች በግብዓትነት ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ጠቁመዋል።   

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም