በእርጅና ያልዛሉ ብርቱ ክንዶች

″የሌማት ትሩፋት″ የእንስሳት፣ የዶሮና የማር ምርቶች በማትረፍረፍ፣ በአረንጓዴ አሻራና በስንዴ የተገኘውን ስኬት በመድገም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ውጥን ነው።

ይህንን መርኃ-ግብር ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ባደረጉበት ወቅት የሌማት ትሩፋት በምግብ ሉዓላዊነት ማስከበርና ክብርን ከማረጋገጥ ጋር የሚቆራኘ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።

የሌማት ትሩፋት መርኃ-ግብር ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን እንድታረጋግጥ ማስቻል፣ በተለይም በሥጋ፣ እንቁላል፣ ማርና ወተት ቅንጦት ሳይሆን ትርፍ ምርት ሆነው እንዲገኙ ለማድረግ ያለመ እንደሆነም ተናግረው ነበር።

ለአራት ዓመታት በሚተገበረው በዚሁ መርኃ-ግብር ዓመታዊ የወተት ምርትን አሁን ካለበት 6 ነጥብ 9 ቢሊየን ሊትር ወደ 11 ነጥብ 7 ቢሊየን ሊትር፣ የዶሮ ሥጋ ዓመታዊ ምርትን ከ90 ሺህ ወደ 240 ሺህ ቶንና የማር ምርትን ከ147 ሺህ ወደ 296 ሺህ ቶን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መርኃ-ግብሩን በአገር አቀፍ ደረጃ በይፋ ማስጀመራቸውን ተከትሎ ከገጠር እስከ ከተማ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ እየተተገበረ ይገኛል።

በዚሁ መርኃ-ግብር የተቀላቀሉ ሁሉ በምግብ እራሳቸውን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ  ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋፅዖ ማበርከት ጀምረዋል። 

በዚህም መርኃ-ግብር ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ዜጎችም ተጠቃሽ ናቸው። 

ከተጠቃሚዎቹ መካከል፤ አቶ ረጋሳ ጉርሙ በዚሁ በአዲስ አበባ ቁስቋም አካባቢ በ1927 እንደተወለዱ ገልጸው፤ አሁን ላይ ወደ 90ዎቹ እድሜ እንደተቃረቡ ይናገራሉ።

አቶ ረጋሳ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ በቁስቋም መጀመሪያ ትምህርት ቤት፣ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ  ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቀለም ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

ከዚህ በመቀጠልም በጎንደር ሜዲካል ኮሌጅ ለአራት ዓመት ትምህርታቸውን በመከታተል በጤና መኮንን በዲፕሎማ ተመርቀዋል።

አቶ ረጋሳ ጉርሙ የኮሌጅ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በተማሩት የሙያና በሌሎችም ዘርፎች በመንግሥትና በግል ተቋማት ከባለሙያነት እስከ ኃላፊነት ለ58 ዓመታት አገራቸውን አገልግለዋል።

ከተማሩበት የሥራ ዘርፍ ውጭ በሥራ አጋጣሚ የተለያዩ ዓለም አገራትን በጎበኙበት ጊዜ በግብርናው ዘርፍ ልምድን እንደቀሰሙም ያነሳሉ።

የ89 ዓመቱ አዛውንት በአዲስ አበባ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸውን አትክልትና ፍራፍሬ በማዘጋጀት በቦሌ አይሲቲ ፓርክ አካባቢ በሚገኘው የእርሻ ማሳቸው  የግብርና ሥራ መጀመራቸውን ይገልጻሉ። 


 

በማሳቸው ከ60 በላይ ዝርያ ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬዎችን ማባዛት፣ የወተት ላሞችን ማራባት፣ በሬዎችን ማድለብ፣ በጎችን ማርባትን ያካተት እንደሆነ ያስረዳሉ። 

የሚከተሉት የግብርና ልማት ጥምር የግብርና ዘዴና ተመጋጋቢ በመሆኑ ውጤታማ እንደሆነ የሚያብራሩት አቶ ረጋሳ፤ ለአገልግሎት የማይውሉ የአትክልትና ፍራፍሬዎች ተረፈ ምርቶችን ለእንሰሳት መኖ፣ ከእንሰሳት የሚገኘውን ቆሻሻ ለተፈጥሮ ማዳበሪያና ለባዮ ጋዝ በመጠቀም ምርታቸውን እያሳደጉ እንደሚገኙ ያስረዳሉ።


 

ከቤታቸው እስከ ማሳቸው ድረስ የከርሰ-ምድር ውኃን በመጠቀም የግብርና ልማቱ ክረምትና በጋ ሳይሉ በስፋት በማልማት እጅን በአፍ የሚያስጭን ውጤት እያስመዘገቡ መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

በግብርና ልማቱ ከ18 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞችን ቀጥረው እንደሚያሰሩ በመጥቀስ፤ ሠራተኞቹ በእውቀትና በክህሎት እንዲሰሩ በማድረግ የቤታቸውን ማዕድ በማትረፍረፍ ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። 


 

ለገበያ ከሚያቀርቡት ከእያንዳንዱ ምርት ላይ ከሌላው ገበያ ሲነጻጸር ከ10 እስከ 20 ብር የሚሆን የዋጋ ቅናሽን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

በቀጣይ ሥራውን በማጠናከር የግብርና ማሳውን የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ የማድረግ ዕቅድንም ወጥነዋል።


 

"ኢትዮጵያ ለም የሆነ መሬትና የውኃ ኃብት ያላት አገር ነች" ያሉት አቶ ረጋሳ፤ ወጣቱ ትውልድ መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሥራ ወዳድነት መንፈስ በመነሳሳት አገሩን በማልማት ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባው መክረዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር)፤ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ እራስን ለመቻል እየተደረገ ላለው ጥረት የከተማ ግብርና ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፤ በአነስተኛ ቦታ ከፍተኛ ምርት ማምረት እንደሚቻል በማሳየት ከሸማችነት ወደ አምራችነት የመሸጋገር ዕድልን እየፈጠረ ነው።

ግብርና ሚኒስቴር በግብርና ኤክስቴንሽን በኩል አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የከተማ ግብርና ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር በምግብ እራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ በመሆኑ፤ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም