ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ በፌዴራል መንግስት የተጀመሩ ነባርና አዲስ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛሉ

ጎንደር፤ ነሐሴ 13/2016 (ኢዜአ)፡-  በጎንደር ከተማ በፌዴራል መንግስት የተጀመሩ ነባርና አዲስ የልማት ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለህዝብ አገልግሎት ለማዋል እየተደረገ ያለው ርብርብ በጥሩ አፈጻጸም  ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ። 

የአማራ ክልልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራር አባላት  የከተማውን የኮሪደር ልማት፣ የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት ዓለም አቀፍ ቅርስ ጥገና እና የአዘዞ ጎንደር የኮንክሪት የአስፋልት መንገድ ስራን ጎብኝተዋል፡፡

በዚህ ወቅት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንደተናገሩት፤ የህዝብን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በከተማው እየተከናወኑ ያሉ የሠላም ማስከርና የልማት ፕሮጀክቶች ስራ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው፡፡

በተለይም በጎንደር  እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገፅታ ለመቀየር ካለው ፋይዳ ባሻገር ለበርካታ ወገኖች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻለ ከጉብኝቱ  መረዳት መቻላቸውን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ከመሆናቸውም በላይ የከተማውን የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንት፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማነቃቃትና በማሳለጥ የጎላ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረዋል፡፡


 

ዓለም አቀፍ ቅርስ የሆነው የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት ጥገና ስራ የቀደምት አባቶችን ታሪካዊ አሻራ ከማስቀጠል ባሻገር የህዝቡን አንድነት፣ መቻቻል፣ አብሮ መኖርንና ወንድማማችነትን ለማጠናከር ሰፊ ጠቀሜታ እንዳለውም አስታውቀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አመራር ሰጪነት በከተማው የተጀመሩት ነባርና አዲስ የልማት ፕሮጀክቶችን በአጠረ ጊዜ በማጠናቀቅ ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታችና በጥሩ  ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለዚህም የክልሉ አመራር አባላት  በየጊዜው የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ለህዝብ ጥቅም አንዲሰጡ ለማድረግ ሠላም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ የከተማው ህዝብ ሠላም ወዳድነቱን አጠናክሮ በመቀጠል ለፕሮጀክቶቹ መሳካት እገዛውን  እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የአማራ ክልል መንገዶች ቢሮ ሃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአዘዞ ጎንደር የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ስራ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ተረክቦ በአዲስ መልክ ግንባታውን ከጀመረ ወዲህ ስራው በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት  ለአስፋልት ማንጣፍ ስራ የሚያግዝ የ3 ኪሎ ሜትር የመንገድ ማስተካካልና ከመንገዱ ርዝመት አንድ ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአስፋልት ማንጠፍ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም 595 ሜትር ርዝመት ያለው የድጋፍ ግንብ ስራ መከናወኑን ጠቁመው፤  አንድ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመንገድ መሃል አካፋይ የኮንክሪት ግንብ ስራ መጠናቀቁንም ገልጸዋል፡፡

የመንገድ ስራው በቀጣዩ ዓመት እስከ ጥምቅት  ድረስ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ ታሳቢ ተደርጎ እየተከናወነ እንደሆነም አስረድተዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ ለመንገድ ግንባታው የሚወሉ የማሽነሪና የግንባታ ቁሳቁሶች ግብዓት አቅርቦት በበቂ ሁኔታ  እንዲሟላ ጥረት መደረጉን አመልክተዋል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር  የመንግስት ኮሙዩኒኬሸን መምሪያ ሃላፊ አቶ አበበ ላቀው እንደገለጹት፤  የልማት ፕሮጀክቶች የከተማውን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት አዎንታዊ ፋይዳ አላቸው። 

የልማት ፕሮጀክቶቹ ከመደበኛ የስራ ሰዓት ውጪ ምሽት ጭምር በፈረቃ እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ አዲስ የስራ ባህልን በማስተዋወቅ በህዝቡ ዘንድም ከፍተኛ መነሳሳትን የፈጠሩ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም