የምስራቅ አፍሪካ አገራት የአርብቶ አደሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መቋቋም መርሐ ግብር ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካ አገራት የአርብቶ አደሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መቋቋም መርሐ ግብር ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 13/ 2016 (ኢዜአ)፦የምስራቅ አፍሪካ አገራት የአርብቶ አደሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መቋቋም መርሐ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ሆኗል።ለመርሐ ግብሩ ማስፈጸሚያ 47 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ እንደሚደረግ ተገልጿል።
የግብርና ሚኒስቴርና የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ቀጣናዊ መርሐ ግብሩን አስመልክቶ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በሰባት የምስራቅ አፍሪካ አገራት የድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች የሚተገበረው መርሐ ግብር የአርብቶ አደሮችና የቁም እንስሳት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ተጽእኖዎች መቋቋም የሚችሉበትን አቅም ማጎልበት ላይ ትኩረቱን ማድረጉን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ፕሮግራሙ ማንዴራ፣ ካራሞጃ፣ ማራ-ሰሬንጌቲና ባህር አል አረብ የተሰኙ ድንበር ተሻጋሪ የክላስተር አካባቢዎች የሚተገበር ሲሆን ክላስተሮቹ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛንያና ዩጋንዳን ይሸፍናሉ።
ለመርሐ ግብሩ ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገውን የ47 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ የአውሮፓ ሕብረት እንደሚሸፍን ተገልጿል። ከዚህም ውስጥ ኢትዮጵያ 6 ነጥብ 25 ሚሊዮን ዩሮ ታገኛለች።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረውን ተጽእኖ በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢዎች ጉዳት የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቋቋም እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለመርሐ ግብሩ ተፈጻሚነት ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ጋር በትብብር እንደምትሰራም አመልክተዋል።
የፋኦ የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ መርሐ ግብሩ ድርጅቱ እየተገበረ ከሚገኘው ስትራቴጂካዊ ማዕቀፍ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕቀፉ ምርታማነትን ማሳደግ፣ የስርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ምቹ ከባቢ አየርና የአኗኗር ዘይቤን መፍጠር ላይ ያተኮረ መሆኑን አመልክተዋል።
የግብርና ሚኒስቴር በመርሐ ግብሩ ትግበራ ላይ ቁልፍ ሚና የሚወጣ ዋንኛ አጋር መሆኑንም ተናግረዋል።
መርሐ ግብሩ በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚያጋጥማቸውን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የመቋቋም አቅም እንደሚያሳድግ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።